በአማራ ክልል ከ319 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ እየለማ ነው።

5

ባሕር ዳር: የካቲት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምርት እና ምርታማነትን ሊያሳድጉ በሚችሉ የቴክኖሎጅ ውጤቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።

በቆቦ ወረዳ አራዶ 08 ቀበሌ አርሶ አደር የኾኑት ዓለሙ አበራ ከዚህ በፊት ማሳቸውን በኩታ ገጠም እርሻ አርሰው እንደማያውቁ አስታውሰዋል።

በሚያገኙት ምርት ቤተሰቦቻቸውን ማሥተዳደር ይከብዳቸው እንደነበርም ነው የነገሩን።

አርሶ አደሩ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግብርና ባለሙያዎች በሚሰጡት ምክረ ሀሳብ በመታገዝ እና የኩታ ገጠም እርሻን ተግባራዊ በማደረግ የበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ውጤታማ መኾናቸውን ገልጸውልናል። ኑሯቸውን ማሻሻላቸውንም አጫውተውናል።

በሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡደን መሪ አለባቸው መርዓዊ ዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 31 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት አቅዶ ከ128 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚኾነው በኩታ ገጠም እርሻ የለማ እንደኾነም ጠቅሰዋል።

አሁን ያለው የሰብል ቁመና ሲታይ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ያመላክታል ያሉት ቡድን መሪው በዘር ከተሸፈነው ማሳም 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ሊገኝ እንደሚችል ነው የተናገሩት።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ አግሮኖሚ ባለሙያው ንጋቴ አለማየሁ ክልሉ ያለውን ፀጋ በመጠቀም በያዝነው በጀት ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ላይ ከ319 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በክላስተር መልማቱን ተናግረዋል።

በዚህም የእቅዱን 91 ነጥብ 3 በመቶ የሚኾነውን ማልማት ተችሏል ነው ያሉት።

የመስኖ ስንዴ ምርቱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ100 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ከለማው የበጋ መስኖ ስንዴ ከ13 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሠበሠባል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።

ይህንንም ውጤታማ ለማድረግ ከ467 ሺህ በላይ ኩንታል ምርጥ ዘር እና 559 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሏል።

በዚህ ሥራ ላይ ከ957 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተሳታፊ ኾነዋልም ብለዋል።

ስንዴ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚ የተሻለ አስተዋጽኦ በማበርከት ከፍተኛውን ሚና የሚጫዎት ሰብል እንደኾነም ገልጸውልናል።

ዘጋቢ፦ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ውጤት ማምጣት ተችሏል።