
ደብረማርቆስ፡ የካቲት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር አይናለም ይላቸው በምሥራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ የአማኑኤል ዙሪያ የወተት ልማት እና ግብይት ኅብረት ሥራ ማኅበር አባል ናቸው።
ከእርሻ ሥራቸው ጎን ለጎን ከአራት ዓመት በፊት በዘመናዊ የወተት ላም እርባታ ሥራ ላይ በመሰማራታቸው የተሻለ ተጠቃሚ እየኾኑ መምጣታቸውን ይናገራሉ።
ሌላው በማቻክል ወረዳ የነጭ ቀበሌ ነዋሪ የኾነው ወጣት መኳንንት ይልቃል ቀደም ብሎ ይሠራ የነበረውን የዶሮ እርባታ ሥራ ወደ ወተት ልማት በማሸጋገር ለማኅበሩ ከሚያቀርበው ወተት በወር ከ100 ሺህ ብር በላይ ገቢ እያገኘ መኾኑን ተናግሯል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ዳኘ ዋሴ በዞኑ ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ አሠራሮችን በማስፋፋት እና በወተት ልማት ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ግንዛቤ በማሳደግ ውጤት ማምጣት ስለመቻሉ ተናግረዋል።
ባለፉት ሰባት ወራት በዞኑ ከ350 ሺህ ቶን በላይ ወተት ለአካባቢው እና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮች እና ወጣቶች ተጠቃሚ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
በዞኑ የተመሠረቱት 20 የወተት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለዘመናዊ የመኖ አጠቃቀም እና ዝርያን ለማሻሻል ለሚደረጉ የድጋፍ እና ክትትል ተግባራት ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን አስረድተዋል።
ኀላፊው ዘርፉን በተደራጀ መንገድ በመምራት ማኅበራት ምርታቸውን በቀላሉ ወደ ገበያ በማቅረብ ያላቸውን የቁጠባ አቅም ከ68 ሚሊዮን ብር በላይ ማሳደግ መቻላቸውን ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
