
ባሕር ዳር: የካቲት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ዘላቂነት ያለው ዕድገትን ለማረጋገጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል።
ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መርሐ ግብር አንዱ ነው። መርሐ ግብሩ ለ10 ዓመት ይዘልቃል። ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ እየተተገበረ ነው።
የኢትዮጵያ ታምርት መርሐ ግብር ከተጀመረ ጀምሮ የፋብሪካዎች የማምረት አቅም፤ የገበያ እና የመሠረተ ልማት ሁኔታ እያደገ መጥቷል። ነገር ግን የመብራት አቅርብቱ ማሻሻል እንደሚገባው አምራቾች ጠይቀዋል።
ካነጋገርናቸው አምራቾች ውስጥ በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙት ዳንኤል አብርሐም ይገኙበታል። ከጥቃቅን እና አነስተኛ ተነስተው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ አምራችነት የደረሱ ናቸው። የባልትና ውጤቶች እና ቅመማቅመም በማምረት ለገበያ በማቅረብ ላይም ይገኛሉ። የመብራት መቆራረጥ ችግር ከተፈታ ደግሞ ወደ ተሟላ የማምረት ሥራ መግባት እንደሚቻል ነው የገለጹት።
ሌላኛው በባልትና ዘርፍ ተሠማርተው እንደሚገኙ የገለጹት ኤፍሬም፣ ዮሐንስ እና ጓደኞቻቸው ማኅበር ተወካይ እንደነገሩን መንግሥት ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ትኩረት መስጠቱ ለሀገር እድገት ከፍተኛ ሚና የሚጫዎት ነው። ፋብሪካዎች በተሟላ መንገድ ወደ ማምረት እንዲገቡ የመብራት አቅርቦትን ማሻሻል ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የባሕር ዳር ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልገግሎት ዳይሬክተር ሸጋው የሻምበል በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙት ሰብስቴሽኖች ከከተማዋ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሲያጋጥም ቆይተዋል ብለዋል።
በከተማዋ የሚገኙ ፋብሪካዎችም በፈረቃ ኃይል የሚያገኙበት መንገድ ተፈጥሮ ቆይቷል ነው ያሉት። ችግሩን ለመፍታት አንድ ተጨማሪ ሰብስቴሽን ግንባታ ሥራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈ የእንጨት ፖሎችን ወደ ኮንክሪት ፖል የመቀየር ሥራ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ 10 ሺህ 500 የሚጠጋ የኮንክሪት ፖሎ መቀየሩን በማሳያነት አንስተዋል። ከካቲት 30/2018 ዓ.ም ጀምሮ በፈረቃ ይቋረጥ የነበረው ኤሌክትሪክ ችግር እንደሚቀረፍም ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
