የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ ሴት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ለመመለስ እየተሠራ ነው።

12

 

ባሕር ዳር: የካቲት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ የሰላም እጦቱ ክፉኛ ጉዳት ካደረሰባቸው ዘርፎች መካከል ትምህርት አንዱ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲነጠሉ አድርጓል። ለሥነ ልቦና ጉዳትም ዳርጓል።

በ2017 በጀት ዓመት ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህር ገበታ ወጭ ኾነው ከርመዋል።

ተማሪ መልካም ቢራራ የማንኩሳ አጠቃለይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ናት። የሰላም እጦት በፈጠረው የትምህርት መስተጓጎል ምክንያት ተማሪዎች ለሥነ ልቦና ጉዳት ተዳርገው እንደነበር ታስታውሳለች።

ከትምህርት መስተጓጎል ባለፈ ሴት ተማሪዎች ለያለ ዕድሜ ጋብቻ እና ለአልተፈለገ የጉልበት ሥራ እንዲጋለጡ አድርጓል ትላለች።

ጓደኞቿም ትምህርት መማር ሲገባቸው ወደ ትዳር በመግባት ልጅ እንዲወልዱ እና ቤተሰብ እንዲመሩ ተገድደዋል ብላለች። የሰላም እጦቱ በሴት ልጆች ሕይወት ይዞ የመጣው ዳፋ ከሚገለጸው እና ከሚታየው በላይ ነው ስትል የውስጧን ስሜት አጋርታለች።

አሁን ላይ በተገኘው አንፃራዊ ሰላም በትምህርት ገበታ እንደምትገኝም ትናገራለች። ነገር ግን አሁንም ቢኾን ትምህርት ያላገኙ ሴት ተማሪዎች አሉ ትላለች። ዘላቂ ሰላም ፀንቶ የመማር ማስተማር ሂደቱ በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ኾኖ እንዲቀጥል መደረግ አለበት ስትልም ጠይቃለች።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የጃቢ ጠናን ወረዳ የትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይልቃል አባባው ችግሩ በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል።

በ2018 የትምህርት ዘመን ይማራሉ ተብሎ ከታቀደው 78ሺህ 671 ተማሪዎች ውስጥ 42ሺህ 774 ተማሪዎች ሴቶች ናቸው ብለዋል። ከእነዚህም ውስጥ 8ሺህ 680 ሴት ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ቢገኙም 34ሺህ 94 ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን ነው ያስረዱት።

ሴት ተማሪዎችን ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ መማር ሲገባቸው ቤተሰብ የመመስረት እንዲሁም ወደ ሌላ አካባቢ ለቀው እንዲሄዱ ይኾነዋል ብለዋል።

በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች ሴት ተማሪዎች ለመማር ተፅዕኖው አሁንም ድረስ መኖሩን ነው የተናገሩት።

የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ እየተሠራ ይገኛልም ነው ያሉት።

ሴት ተማሪዎችን የሥነ ልቦና ግንባታ እና የምክር አገልግሎት በመስጠት ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት። ሴት ተማሪዎችን በትምህርት ገበታ ለማስቀጠልም ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ነው ያስረዱት።

ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በተያዘው በጀት ዓመት 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገበ ታቅዶ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች መመዝገብ ተችሏል። ከ3 ነጥብ 1ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ደግሞ ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ በክልሉ ከ1ሺህ 400 በላይ ትምህርት ቤቶች እስከአሁን አልተከፈቱም ብለዋል።

አንፃራዊ ሰላም በተገኘባቸው አካባቢዎች ከማኅበረሰቡ እና ከሚመለከተው አካል ጋር ውይይት በማድረግ የመማር ማስተማር ሂደቱ እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

ዘግይተው የጀመሩ ትምህርት ቤቶችም የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሠጠ ነው ብለዋል። ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲለዩ ከተደረጉ በሀገር ዕድገት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ነው ያሉት።

የሴት ተማሪዎችን ተፅዕኖ ለመከላከል እና በትምህርት ገበታ ለማስቀጠል ልዩ ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ ይገኛልሞ ብለዋል።

የሴቶችን የወደፊት ተስፋ ከፍ ለማድረግ ሁሉም ይመለከተኛል በሚል ለትምህርት ትኩረት መስጠት እንደሚገባውም ነው ያስገነዘቡት።

የዛሬ ተማሪዎች የነገ ሀገር ተረካቢ እና የወደፊቷን ኢትዮጵያ የሚወስኑ በመኾናቸው ለትምህርት ሥራ ሁሉም በጋራ መሥራት ይገባዋል መልዕክታቸው ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየምርጫ ሥራ የምርጫ ቦርድ ብቻ ሳይኾን የጋራ ሥራ ነው።
Next articleየትምህርት ተደራሽነት ሽፋንን ከማሳደግ አኳያ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል።