
ባሕር ዳር: የካቲት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ሁሴን ኑሩየ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነዋሪ ናቸው። በግጭት ምክንያት የእርሳቸውን ጨምሮ የሰባት ልጆቻቸው ንብረት ወድሞባቸዋል። የነበራቸው የእህል ወፍጮ፣ የእንስሳት ሃብታቸው፣ ቤት ንብረታቸው መውደሙ እና መዘረፉ ለሁለት ዓመታት ከቀያቸው ተፈናቅለው እንዲቆዩ አድርጓቸዋል።
ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚያወጣ የሱቅ ንብረታቸውም ተዘርፏል ።
ግጭት በቤተሰባቸው ላይ ያደረሰው የኢኮኖሚ እና የሥነ ልቦና ጫና ጭንቀት ውስጥ የጣላቸው ሲኾን ከማኅበራዊ ሕይወት ተነጥለው እንዲቆዩም አድርጓቸዋል።
አሁን ላይ በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መኖሩን አንስተው ወደ ቀያቸው ተመልሰው ከምንም በመነሳት ምርት እያመረቱ የጠፋባቸው ንብረት በመተካት ላይ መኾናቸውን ለአሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ተናግረዋል።
ግጭት አዕምሮን የሚጎዳ፣ የሥነ ልቦና ጫና የሚያሳድር መኾኑን ገልጸው ከግጭት መራቅ እና ሰላምን ማጽናት እንደሚገባ መክረዋል።
የአቶ ሁሴንን ታሪክ ለአብነት አነሳን እንጅ በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚፈጠሩ ግጭቶች ሰብዓዊ ጉዳት አድርሰዋል፤ ንብረት እንዲወድም አድርገዋል፤ ሰዎች እንዲፈናቀሉ እና መሠረተ ልማቶች እንዲወድሙ አድርገዋል።
ጦርነት፣ ግጭት፣ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች በሰው ልጅ ሕይወት ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን ያስከትላሉ። እነዚህ አደጋዎች ከሚያደርሷቸው ጉዳቶች መካከል የአዕምሮ ቁስለት ደግሞ አንዱ ነው።
የአዕምሮ ቁስለት የሰውን ልጅን የሚዳሰስ እና የማይዳሰስ የአዕምሮ ክፍል የሚያጠቃ መኾኑን በጎንደር ዩኒቨርስቲ ሥነ አዕምሮ ትምህርት ክፍል የክሊኒካል እና ማኅበረሰብ አቀፍ ስፔሻሊስት እና መምህር ጎሹ ኔንቆ ገልጸዋል።
በአዕምሮ ላይ ተቀርጸው የሚቀሩ የማይረሱ ጠባሳዎች በሚያደርሱት ተጽዕኖ አንድ ሰው ሰብዓዊ ጉዳት ሲያደርስ፤ አሉታዊ አስተሳሰብ ሲያሳይ፣ በቀል እና ቂምን ሲያራምድ፤ ከደስተኛነት ሲርቅ፤ ነገሮችን በቀላሉ አለመረዳት፤ ሰዎችንና አካባቢን መርሳት እና ድባቴ ሲከሰቱ በሕክምና ዘንድ የአዕምሮ ቁስለት ተከስቷል ተብሎ እንደሚወሰድ መምህሩ አንስተዋል።
በሰውነት ውስጥ ያለ የጭንቀት ሆርሞን መጠን ሲጨምር እና ስሜት መቆጣጠሪያ ሆርሞን ሲቀንስ ድባቴ፣ አሉታዊ አስተሳሰብ፣ ጨለምተኝነት እና ሌሎች የአዕምሮ ጉዳቶች እንደሚከሰቱ ነው የገለጹት።
ሰው ከራሱ ጋር፤ ሰዎች ከሰዎች፤ ማኅበረሰብ ከማኅበረሰብ፤ ሀገር ከሀገር የሚደረጉ ግጭቶች የአካል፣ የስብዓዊ፣ የቁሳዊ እና የሥነ ልቦና ጫና በማድረስ የአዕምሮ ቁስለት እንዲፈጠር ያደርጋሉ።
በግጭት ወቅት የሚከሰቱ ጾታዊ ጥቃቶች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የአዕምሮ ቁስለትን የሚፈጥሩ እንዲሁም በማገገም ላይ የነበሩ ሕመምተኞችን መልሰው ለአዕምሮ ቁስለት የሚዳርጉ እና የመዳን ሂደታቸውን የቁልቁለት ጉዞ የሚያደርጉም ናቸው።
ሰው ከራሱ ጋር የሚያደርገው ግጭት ትልቅ የኾነ የአዕምሮ ቁስለት እና የሥነ ልቦና ጫና ያደርሳል። የአዕምሮ ቁስለት በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋዎች እንደሚፈጠርም ተናግረዋል።
በግጭት ወቅት የሚከሰቱ ስደት እና መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት የሰብዓዊ ጉዳቶች የአዕምሮ እክልን ያስፋፋሉ፤ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች እንዲከሰቱ ያደርጋሉ ብለዋል። ከጭንቀት ለመራቅም በርካቶች ወደ ሱስ ሕይወት ይገባሉ ነው ያሉት።
ውስጣዊ ግጭት ለትልልቅ ጦርነቶች መነሻ ሊኾን እንደሚችል ያነሱት መምህሩ የሰዎችን ሰብዓዊ መብት በመጣስ የሚደሰቱ ሰዎች የሽብር ጥቃት በመፈጸም በሚመሩት ተቋም ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ ማኅበረሰብን እና ሀገርን ወደ ግጭት በማስገባት ለትላልቅ ጦርነቶች መንስኤ እንደሚኾኑ ነው የገለጹት።
በግጭት ወቅት እና ከግጭት በኃላ ከ100 እስከ 70 በመቶ ጭንቀት፣ ከ67 በመቶ በላይ ድባቴ፤ ከ42 በመቶ በላይ ከግጭት በኃላ የአዕምሮ እክል እንደሚገጥማቸው አንስተዋል።
የተጋነነ ፍርሃት፤ የእንቅልፍ እጦት፤ የስሜት መዋዠቅ፤ የሰውነት አለመታዘዝ፤ ትኩረት አለማድረግ፤ የግጭት ምስሎችን በአዕምሮ ደጋግሞ ማየት፤ አሉታዊ አስተሳሰብ ማራመድ፤ ጨለምተኛ መኾን፤ ተስፋ መቁረጥ፤ የትውስታ ማጣት፤ ራስን አብዝቶ መውቀስ፤ የምግብ ፍላጎት ማጣት እና የተጋነነ የልብ ምት የአዕምሮ ቁስለት ምልክቶች ናቸው ብለዋል መምህሩ።
የአዕምሮ ቁስለት ሲከሰት የመድኃኒት እና የሥነ ልቦና የሕክምና አማራጮች እንደሚሰጡ መምህር ጎሹ ገልጸዋል። ሕክምናዎቹ በአጭር እና በረጅም ጊዜ ለውጥ የሚያሳዩም ናቸው።
በግጭት ወቅት የሚከሰት የአዕምሮ ቁስለት ግለሰብን ብቻ ሳይኾን ማኅበረሰብን የሚያጠቃ በመኾኑ የተጎዱ ሰዎችን መልሶ በማቋቋም፤ ወደ ሌሎች ቦታዎች በማስፈር፤ ማኅበራዊ ትስስሮችን በመፍጠር እና የሕይወት ክህሎት ሥልጠናዎችን በመስጠት ማከም እንደሚቻልም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ማኅበረሰቡ ላይ ጫና እያሳደሩ በመኾናቸው መጠቋቆምን በማራቅ እና ወደ ራስ በመመልከት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል። ከዝምታ ይልቅ ማግባባት ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግም መክረዋል።
ውስጣዊ ሰላምን በመጠበቅ እና ሚዛናዊ አመለካከትን በመያዝ የአዕምሮ ቁስለትን መከላከል እንደሚቻልም አንስተዋል።
ማኅበረሰቡ በግጭት የሚከሰትን የአዕምሮ ቁስለት ችግርን የሚቋቋም ስብዕናን በመገንባት፤ ሚዛናዊ አስተሳሰብ በመያዝ፤ ከሰዎች ጋር በማውራት፤ ችግርን ለሌሎች በማካፈል እና መንፈሳዊ ቦታዎች ላይ ጊዜን በማሳለፍ ከጭንቀት መራቅ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
