“እንደ ቀልድ የጀመርኩት ሱስ…”

9
ባሕር ዳር: የካቲት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሱስ አንድን ነገር በተደጋጋሚ መጠቀም እና የሰውነት አካል ለዚያ ነገር ተገዥ ወይንም ጥገኛ መኾን ነው።
ሰዎች አነቃቂ ወይንም አደንዛዥ ንጥረ ነገሮችን በተደጋጋሚ ሲጠቀሙ፣ የመጠቀም ጊዜያቸው ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲመጣ ጎጅ ሱስ ተብሎ እንደሚጠራ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
የሚጠቀሙት ሱስ አካላዊ፣ አዕምሯዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ሲያመጣ፣ ሥራቸውን በአግባቡ መወጣት ሲያቅታቸው እና ጫናውን እያወቁ ለማቆም ከተቸገሩ ከፍተኛ ሱስ ውስጥ እንደገቡ ያሳያል።
በአማራ ክልል በተለያዩ ሱሶች የተጠቁ ዜጎችን ሕክምና ለመስጠት የሚያስችል ማገገሚያ በደብረ ታቦር ከተማ ተቋቁሞ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። በማዕከሉ ካገኘናቸው ወጣቶች ውስጥ ዳንኤል ያየውሰው አንዱ ነው። ዳንኤል ያየውሰው ለ14 ዓመታት ያህል በሱስ ውስጥ እንደቆዬ ነው የገለጸልን።
ወደ ሱሱ የገባው ደግሞ የ12ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት ነበር። “የጀመርኩት እንደቀልድ ነበር” ሲል ይናገራል። የከፍተኛ ትምህርት ውጤት አስመዝግቦ ወደ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ እንደተቀላቀለ ደግሞ የመጠጥ እና የአደንዛዥ እጽ ተጠቃሚነቱ እየጨመረ መጣ። በወቅቱ በሱሱ ምክንያት በተፈጠረ ችግር ለእስር ተዳረገ። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱንም አቋረጠ፤ ከእስር እንደተለቀቀ የቤተሰብ ጥገኛ ለመኾን ተገደደ። እየቆዬ ሲሄድ ደግሞ ከቤተሰብ እና ከሌሎች ሰዎች ጋር ግጭት ውስጥ ገባ። ከማኅበራዊ ሕይወትም ተገለለ።
ችግሩም እየባሰ ሲሄድ በቤተሰብ ርዳታ አማካይነት በደብረ ታቦር ከተማ በሚገኘው የማገገሚያ ማዕከል ሕክምና እንዲከታተል ነበር የተደረገው። በማዕከሉ ከአንድ ወር በላይ የሥነ ልቦና እና አካላዊ ሕክምና እንደተደረገለት ገልጾልናል። ከዚህም በተጨማሪ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል፤ ከስፖርት በኋላ በተለያዩ መዝናኛዎች ጊዜውን ያሳልፋል።
የተለያዩ ሥዕሎችንም ይስላል፤ መጽሐፍም ያነባል። አሁን ላይ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛል፤ ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅሎ መደበኛ ሥራውን ለማከናወን ራሱን ማዘጋጀቱንም ገልጾልናል።
“እንደ ቀልድ ጀመርኩት” ባለው ሱስ ሁሉ ነገሩን እንዳጣ በቁጭት ይናገራል። ነገን የተሻለ ለመኖር ራስን መግዛት፣ ራስን መኾን እና የአቻ ተጽዕኖን መቆጣጠር ከወጣቶች እንደሚጠበቅም መክሯል።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የሱስ ማገገሚያ ማዕከል የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት ጋሻው ምኅረት (ዶ.ር) እንዳሉት የሱስ ተጠቂዎች ማዕከሉን እንደተቀላቀሉ ለሁለት ወር እና ከዚያ በላይ የግል እና የቡድን የሥነ ልቦና እና የመድኃኒት ሕክምና ይሰጣል። የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲያከናውኑ ይደረጋል።
በተለያዩ መዝናኛዎች እንዲያሳልፉ ማድረግ ሌላኛው መንገድ መኾኑን አንስተዋል። አጠቃላይ ስለሱስ ምንነት፣ ስለጉዳቱ፣ ከሱስ አገግመው ሲዎጡ ሊያጋጥማቸው ስለሚችሉ ጉዳዮች ትምህርት ይሰጣል። መጨረሻ ሲወጡ ደግሞ የቤተሰብ የሥነ ልቦና ሕክምና ተሰጥቷቸው እንዲወጡ ይደረጋል ነው ያሉት።
ባለሙያው እንዳሉት ሱስ እንደ ሌሎች በሽታዎች ታክሞ የሚድን ቢኾንም በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ሕመም ስለማይቆጠር ተጠቂዎችን ወደ ሕክምና የማምጣት ችግር ይታያል። ወደ ማገገሚያ የሚገቡት ደግሞ ወጣቶች እና የማልማት አቅም ያላቸው መኾናቸውን ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል ነው ያሉት። ሱስ ከግለሰብ ችግር ባለፈ በሀገር ላይ የሚያደርሰው ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ኪሳራው ከፍተኛ በመኾኑ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሃይማኖታዊ ተቋማት እና መንግሥት በተቀናጀ መንገድ እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
ሱስ የባሕርይ እና የንጥረ ነገር ተብሎ በዋናነት የሚመደብ ነው። እንደ ሲጋራ፣ አልኮል፣ ጫት፣ ትራማዶል፣ ካናቢስ የመሳሰሉት ከንጥረ ነገር ሱስ ይመደባሉ። እንደ ቁማር፣ የኢንተርኔት ወይንም ሶሻል ሚዲያ የመሳሰሉት ደግሞ ከባሕርይ ሱስ እንደሚመደቡ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleተማሪዎች በክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየተሠራ ነው።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክትን ጎበኙ።