ተማሪዎች በክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየተሠራ ነው።

4
ደብረ ማርቆስ: የካቲት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ቤተልሄም አዱኛ እና ሞላ ጌትነት በደብረ ማርቆስ ከተማ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡
በክልል አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉን አቀፍ ጥረት እያደረጉ መኾናቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
መምህራንም ቅዳሜ እና እሑድን ጨምሮ ባሉ ትርፍ ጊዜያቸው እገዛ እያደረጉላቸው መኾኑን ይገልጻሉ፡፡ ይህም ለላቀ ውጤት እንደሚያበቃቸው ተናግረዋል፡
የንጉስ ተክለ ሃይማኖት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ዋልተንጉስ አያሌው በትምህርት ዘመኑ ቅድመ አንደኛ ደረጃን ጨምሮ ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብለው እያስተማሩ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
መምህራን ትርፍ ጊዜያቸውን መስዋዕት በማድረግ ተማሪዎች በክልል እና በሀገር አቀፍ ፈተናዎች ለተሻለ ውጤት እንዲበቁ ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡ ተማሪዎች ቅዳሜ እና እሑድን ጨምሮ ቀኑን ሙሉ የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እንዲያገኙ ስለመደረጉም አንስተዋል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ ስር ከሚገኙ 49 አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 40 በሚኾኑት እና በአራት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራው እየተከናወነ መኾኑን የገለጹት ደግሞ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ብርሃን አንተነህ ናቸው፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ርብርብ እየተደረገ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው ዝቅተኛ የትምህርት አቀባበል ያላቸውን ተማሪዎች ለይቶ የመደገፍ እና የባከኑ ክፍለ ጊዜዎችን በልዩ ሁኔታ የማካካስ ሥራ በትኩረት መሠራቱንም አመላክተዋል፡፡
ከ3ሺህ 700 በላይ የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል እንዲሁም ከ1 ሺህ 800 በላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ለማብቃት እየተሠራ ነው ያሉት ኀላፊው መምህራን የተቃራኒ ፈረቃን እና ትርፍ ጊዜያቸውን በመጠቀም ለተማሪዎች ልዩ ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተናውን በበይነ መረብ እንዲወስዱ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን እያከናወኑ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የቄጦ የመስኖ መሠረተ ልማት ፕሮጀክትን ጎበኙ።
Next article“እንደ ቀልድ የጀመርኩት ሱስ…”