
ባሕር ዳር: የካቲት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወርሃ የካቲት ሲነሣ ቀድሞ የሚመጣው የካቲት 23/1888 ዓ.ም የተገኘው የዓድዋ ድል ነው። ይህ ድል ለዘመናት ሊወሳ በጥቁር ሕዝቦች ደም ተጽፎ እና በብዕር ተከትቦ እንደሚገኝ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
ለድሉ ትልቅ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ሴቶች በግንባር ቀደም የሚጠቀሱት ጥበበኛ፣ ብልህ እና አስተዋይ ሴት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ሁሌም ሥራቸው ጎልቶ ይታያል።
እቴጌ ጣይቱ ሴትነት ሳይበግራቸው ለቆሙበት ዓለማ በመጽናት ለሀገራቸው ትልቅ ስኬት አስመዝግበው አልፈዋል። በየዘመናቱ ትውልድ እየዘከራቸው እና እየዘመረላቸው እንደሚገኝ ታሪክ ያስረዳናል።
እቴጌ ጣይቱን እንደ ምሳሌ አነሳን እንጂ በርካታ ሴቶች በየዘመናቸው ለሀገራቸው አስተዋጽኦ ያበረከቱ እና በተሠማሩበት ስኬታማ ሴቶች እልፍ ናቸው።
ሴቶች በየተሠማሩበት የሥራ መስክ ስኬታማ ለመኾን ከእቴጌ ጣይቱን ምን ይማራሉ?
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር መምህር ናቸው አስቴር ሙሉ (ዶ.ር) ከዲፕሎማ ኤክስቴንሽን የትምህርት ደረጃ ተነስተው አሁን ላይ ሦስተኛ ዲግሪ ወይም የዶክትሬት ማዕረግ ባለቤ እንደኾኑ ታሪካቸውን አጫውተውናል።
ስለ ስኬት ምስጢራቸው እንዳሉት “ወላጅ እናቴ በልጅነቴ ትልቅ ደረጃ እንድደርስ ትመክረኝ ነበር። ከዚያም የእናቴን ህልም እውን ለማድረግ እና ምክሯን ለመተግር ጠንክሬ መሥራት ጀመርኩ” ይላሉ።
የሚገጥሙ ውጣ ውረዶችን በጥንካሬ በማሸነፍ የወላጅ እናታቸውን ራዕይ እውን አድርገዋል። የልጀነት ህልምን በአላማ እና በጽናት ለስኬት በቅተው ልጆችን አፍርተው ደስተኛ ኾነው ኑሮን እንደሚገፉ ነው የሚናገሩት።
ቤተሠብ መምራት ግን ከስኬት አንዳላገዳቸው እና ባለቤታቸውም ከጎናቸው እንደኾኑ ይገልጻሉ። ከማስተማር ባለፈም ድርብርብ ኀላፊነትን በብቃት እየተወጡ ነው።
ለረጀም ዓመት በመምህርነት ሙያ በመሥራት በርካታ ተማሪዎችንም አፍርተዋል። በቀጣም ከማስተማር ባለፈ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን ለመሥራት ሰንቀዋል።
እቴጌ ጣይቱ ሀገር ወዳድ ጠንካራ እና አርቆ አሳቢ ሴት ናቸው ይላሉ ዶክተር አስቴር። የሴትነት ጥበብ እና አስተዋይነትን በመጠቀም በተሠማሩበት ስኬታማ ኾነው ለሌሎች ሴቶች አርዓያ ኾነው አልፈዋል ነው ያሉት።
በየዘመናቱም በርካታ ሴቶች ለዓላማቸው ቆመው ስኬታማ ኾነዋል ብለዋል ዶክተር አስቴር። አሁን ላይ ያሉ ሴቶችም ሴትነት ሳይበግራቸው በዕቅድ እና በዓላማ ብሎም በጽናት ስኬታማ ለመኾን ከጠንካራ እና ስኬታማ ሴቶች መማር ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ሴቶች ድርብርብ ኀላፊነት አለባቸው የሚሉት ዶክተር አስቴር ይህንም በስኬት መምራት የሚቻለው በጉዞ ሂደት የሚገጥሙ ፈተናዎችን በጥንካሬ ማለፍ ሲቻል ነው ብለዋል።
ስኬትን ከግለሰብ አልፎ ለማኅበረሰብ እና ለሀገር በማሰብ ኀላፊነትን መወጣት እንዳለባቸውም ነው ያስረዱት።
ሴቶች “ሴትነት ፆታ እንጂ ከየትኛውም ስኬት እንደማያግድ መረዳት ይገባል” ይላሉ። ሴት ነኝ እችላለሁ፤ ኀለፊነቴን በሚገባ እወጣለሁ፤ ለሀገሬ የበኩሌን አሻራ አስቀምጣሁ ማለት ያስፈልጋልም ብለዋል።
ሴቶች ሀገርን በመውደድ በጋራ የመሥራት ልምድን በማዳበር ለተሰለፋበት ዓላማ በጽናት መቆም እና የስኬት አርበኞች መኾን ይገባል ምክረ ሃሣባቸው ነው።
ዘጋቢ፦ ሥራው ድንቅ ደሳለው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
