
ወልድያ: የካቲት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን የወርቄ – ያያሁሞ – አራቱ ጋሪያ መንገድ የአፋርን እና የአማራን ሕዝብ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ያጠናክራል ተብሎ ታምኖበታል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር መንገድ ግንባታው 17 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን መኾኑን ገልጸዋል።
ከክልሉ መንግሥት የገጠር ትስስር ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም እና ከዓለም ባንክ በጀት በተገኘ 61 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተጀመረ ነው ያስረዱት።
የመንገድ ግንባታው አማራ ክልል ራያ ቆቦ ወረዳን ከአፋር ክልል ዞን አራት አውራ ወረዳ ጋር የሚያገናኝ ነው። የአማራ እና የአፋርን ሕዝብ የገበያ ትስስሩን በማጠናከር፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተደራሽነትን በማስፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የመንገድ ግንባታው በታቀደው ጊዜ እንድዲጠናቀቅ በቅርበት ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት።
መንገዱ የሚሠራበት አካባቢ ነዋሪዎችም ከአፋር ሕዝብ ጋር ግንኙነታቸውን ይበልጥ እንደሚያጎለብት ተናግረዋል። የወርቄ – ያያሁሞ ቀበሌ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ጉዳት የደረሰበት አካባቢ ነው።
የመንገድ ሥራው በ2008 ዓ.ም ከጎብዬ አራቱ ጋሪያ ድረስ ለመሥራት እቅድ ወጥቶለት 35 ኪሎ ሜትር ከተሠራ በኋላ ሥራው ተቋርጦ ነበር። የመንገድ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ኤምቲኤ ኮንስትራክሽን እና አስመጭ ድርጅት ውል እንደወሰደ ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
