
ባሕር ዳር፡ የካቲት 10/2018ዓ.ም (አሚኮ) ረጅም ዘመናትን የዘለቀው ወዳጅነት አጋምዷቸዋል። በተለይም በባሕል እና በኢኮኖሚ ያላቸው ቁርኝት ግንኙነታቸውን ዘመን አይሽሬ አድርጎ እስከዛሬ አዝልቆታል። የቱርክዬ እና የአፍሪካ ቀንድ ፈርጧን ኢትዮጵያ።
በ16ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የሚመዘዘው ግንኙነታቸው የሁለቱ ሀገራትን ጠንካራ መሠረት ያለው ግንኙነት አጉልቶ ያሳያል። ሁለቱ ሀገራት በቀይ ባሕር አካባቢ በነበራቸው ተጽዕኖ እና ፍላጎት እርስ በእርስ ተቀራርበው እንዲሠሩ አድርጓቸዋል።
ቱርክዬ በዘመነ ኦቶማን በቀይ ባሕር ላይ አብሮ ለመሥራት ከነበራቸው ፍላጎት በመነጨ ወደ ኢትዮጵያ ጎንደር ድረስ በመምጣት ከአጼ ፋሲለደስ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ለማድረግ አስገድዷቸዋል።
ቱርክዬ እና ኢትዮጵያ የአንድ ወቅት ግንኙነት ብቻ ያላቸው ሀገራት አይደሉም በንጉሰ ነገስቱ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ቱርክዬ አፍሪካን ለመያዝ ኢትዮጵያን መያዝ ወሳኝ እንደኾነ በመረዳት ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት የመጀመሪያውን ኤምባሲ መክፈት ስትሻ ተመራጭ ያደረገችው ኢትዮጵያን ነበር። ይህም ዘመኑ እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን 1912 ነበር።
ይህም ግንኙነት ሁለቱን ሀገራት በባሕል እና በኢኮኖሚ በማስተሳሰር የነበረው ሚና ከፍ ያለ ነበር። ሁለቱ ሀገራት በባሕል ቡድናቸው አማካኝነት የፈጠሩት የእርስ በእርስ ግንኙነት ሀገራቱ ግንኙነታቸው እንዲያድግ ስለማድረጉም ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
በተለያየ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው መዋዕለ ንዋያቸውን ካፈሰሱ ባለሃብቶች ውስጥ ከቻይና ቀጥሎ ቱርካውያን ቀዳሚዎች ናቸው።
በኢትዮጵያ ላይ በፈጠሩት የሥራ ዕድል ደረጃ በሀገሪቱ ጠንካራ ግንኙነት የፈጠሩት የቱርክዬ ኢንቨስተሮች ትርጉም ያለው ለውጥ በማምጣትም እውነተኛ ወዳጅ አስብሏቸዋል።
በተለይም በጨርቃ ጨርቅ፣ በግንባታ እና በኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ቱርክዬዎቹ በኢትዮጵያ በስፋት እየተሳተፉም ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ካላት ሁለንተናዊ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ አንጻር ሁነኛ ሀገር ናት። ቱርክዬም ቢኾን በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ትኩረት ሰጥታ በመሥራቷ በአፍሪካ ቀንድ ጂኦ-ፖለቲካ ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላት ሀገር ኾናለች።
ኢትዮጵያ የቀጣናው የኢኮኖሚ እና የጸጥታ ማዕከል በመኾኗ ቱርክዬ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የአፍሪካ በር እየተባለች የምትጠራውን ኢትዮጵያን መወዳጀት የግድ ይላታል።
ቱርክዬ በአፍሪካ ቀንድ በሶማሊያ፣ በጅቡቲ እና በኢትዮጵያ ያላት ተሳትፎም ትልቅ ነው። በተለይም በትምህርት፣ በሰብዓዊ ድጋፍ እና በማኅበራዊ ዘርፍ ከፍ ያለ አበርክቶም ያላት ሀገር ናት።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ቱርክዬ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በቀጣናው ሀገራት በወታደራዊ ትብብር፣ በቴክኖሎጅ እና መሰል ጉዳዮች ላይ ትልቅ አበርክቶ ያላት ሀገር መኾኗ ሁለቱ ሀገራት ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው እንዲኾኑ አድርጓቸዋል።
ቱርክዬ የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት መብትን በቅጡ በመገንዘብ በዚሁ ዘርፍ ሀገሪቱ ጥያቄዎቿ እንዲመለሱ በማደራደር በኩል ጥረት ከሚያደርጉት መካከል ተጠቃሿ ናት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
