
አዲስ አበባ: የካቲት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 4ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።
በራስ ምርት የሀገርን እድገት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያመጣ ተብሎ ለ10 ዓመት የተዘጋጀ ስትራቴጂ በመኾኑ ሥራው በውጤት እየታጀበ መቀጠሉን የተናገሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ናቸው።
የሀገራት ሕልውና ከማምረት ጋር የተያያዘ ነው ያሉት ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ ምርት ሥራ ትኩረት በመስጠት እና አምስተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮትም በመቀላቀል የሀገርን ምርት ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ አመርቂ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች ነው ያሉት።
ባለፉት አራት ዓመታት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የኢትዮጵያን የማምረት አቅም ለማሳደግ በተሠራ ተግባር በመጀመሪያው ዓመት የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 46 በመቶ ብቻ የነበረ ሲኾን አሁን ደግሞ ወደ 66 ነጥብ 3 በመቶ የማምረት አቅም አድጓል ብለዋል።
በግማሽ ዓመቱ የገቢ መጠኑም ከ2 ቢሊዮን ወደ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር እድገት አሳይቷል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
በተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት በሀገር ውስጥ በማምረት የመተካት ሥራ መሥራት ተችሏል ብለዋል።
በዚህም የሚጠበቁብንን ሥራዎች በማከናወን ኢትዮጵያን የአፍሪካ ብልጽግና ተምሳሌት እናደርጋለን ያሉት አቶ መላኩ ከዚህ በፊት የነበሩ ኤክስፖዎች ጥሩ ልምድ የተገኘባቸው መኾኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ባለፉት ዓመታት የግብይት ሥረዓቱ እያደገ የመጣ ሲኾን በተለይም በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ መገበያየት ለእድገቱ የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
በአራተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖም ቀድሞ ከነበረው በተሻለ እና ባደገ መልኩ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ለኤክስፖው ውጤታማነት እና ስኬታማነት በየደረጃው ያለ መዋቅር፣ ባለሃብቶች፣ የሚዲያ አካላት እና መላ ሕዝቡ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
