
ባሕር ዳር: የካቲት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እና ሁለተኛው የጣሊያን-አፍሪካ መሪዎች ሥብሠባ የሀገሪቱን አዳዲስ ገጽታዎች ባስተዋወቀ መልኩ በስኬት ማዘጋጀቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ድኤታ እና የብሔራዊ የዝግጅት ኮሚቴ ሠብሣቢ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ የጉባኤዎችን በስኬት መጠናቀቅ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በጉባኤው የ41 ሀገራት መሪዎች፣ የ48 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና 12 ቀዳማዊ እመቤቶችን ጨምሮ ከ20 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ እንግዶች ተካፍለዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) ከልዩ ልዩ ሀገራት መሪዎች እና አቻዎቻቸው ጋር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይቶችን ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
ከ1ሺህ 225 በላይ የሚዲያ ባለሙያዎች በተገኙበት በዚህ መድረክ ኢትዮጵያ ታላላቅ ዓለምአቀፍ ጉባኤዎችን በላቀ መስተንግዶ የማስተናገድ ብቃቷን እና በጎ ገጽታዋን ማሳየት መቻሏን ነው የገለጹት።
ከቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ እስከ ማረፊያ ሆቴሎች ድረስ ደረጃውን የጠበቀ የክብር አቀባበል እና አሸኛኘት መደረጉንም አንስተዋል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ለጉባኤው ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
