
ደሴ: የካቲት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ሀርቡ ከተማ አሥተዳደር የኮሪደር ልማት ማስጀመሪያ መርሐግብር ተካሂዷል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም የነበረው የአካባቢው የትራፊክ ፍሰት የተጨናነቀ እና ለነዋሪዎች ምቹ እንዳልነበር አንስተዋል። የኮሪደር ልማት መሠራቱ ችግሩን ያቃልላል ብለዋል።
የሀርቡ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሙሐመድ ሹመት
ዛሬ የተጀመረው የኮሪደር ልማት በመጭው ታኅሣሥ ወር 2019 ዓ.ም ሠርቶ ለማጠናቀቅ በዕቅድ ተይዟል ነው ያሉት። በመንግሥት እና በማኀበረሰቡ ተሳትፎ 134 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙንም ጠቁመዋል።
የመጀመሪያውን ምዕራፍ እስከ መጭው ግንቦት ወር ድረስ ለማጠናቀቅ ጊዜ ተቆርጦለታል። የኮሪደር ልማቱ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገድ፣ የአረንጓዴ ቦታዎች እና የመዝናኛ ስፍራዎችን ያካተተ መኾኑንም ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን በዞኑ አራት ከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መኾኑን አንስተዋል።
በከተማም ኾነ በገጠር ኮሪደር ልማት ማኅበረሰቡ ኮንቴነር እና ቤቶችን ያለካሳ ክፍያ ከማፍረስ ጀምሮ ባለሃብቶች፣ ነጋዴዎች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች የገንዘብ እና የጉልበት አስተዋጽኦ እያበረከቱ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በሀርቡ ከተማ የሚሠራው የኮሪደር ልማት በአጭር ጊዜ እና በጥራት ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ በከተሞች ብቻ የተወሰነ አይደለም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በወረዳዎች ላይ የገጠር ሽግግር የሚል ዕቅድ ተይዞ የገጠር ኮሪደር ልማት ለመጀመር ዝግጅት መጀመሩንም ጠቁመዋል።
የኮሪደር ልማት ከተሞችን ውብ፣ ጽዱ እና ለነዋሪዎች ምቾትን ከመፍጠር ባሻገር ኢኮኖሚውን በማነቃቃት፣ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና የሥራ ዕድል በመፍጠር የላቀ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ፊኒክስ ሀየሎም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
