
ባሕር ዳር: የካቲት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞለት በ2012 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ከኮኮብ መስክ-መርሐቤቴ (ዓለም ከተማ) የአስፋልት መንገድ ከተጀመረ ዓመታትን ቢያስቆጥርም እስካሁን አልተጠናቀቀም።
ለመኾኑ መንገዱ አሁን ምን ደረጃ ላይ ነው?
የዓለም ከተማ ነዋሪው አቶ ደሳለኝ ወንድምነው የኮኮብ መስክ መርሐቤቴ መንገድ ከተጀመረ ዓመታትን ቢያስቆጥርም እስካሁን አለመጠናቀቁን ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ አልፎ አልፎ መንገዱን የመቁረጥ ሥራ ተጀምሮ የነበረው መንገድ ፈራርሶ ለአገልግሎት አስቸጋሪ እንደኾነም ጠቁመዋል።
‘’የተሻለ መንገድ ይሠራል ብለን ስንጠበብቅ የነበረው ፈረሰብን’’ ያሉት አቶ ደሳለኝ በጉዞ ላይ በተለይም በክረምት ጭቃ ስለሚይዘው መንገዱ አስቸጋሪ መኾኑን ነው የገለጹት።
ማኅበረሰቡ በመንገዱ አስቸጋሪነት ምክንያት ከመደበኛው የትራንስፖርት ታሪፍ በእጥፍ እንደሚከፍል እና እህል ለመጫን ለኩንታል እስከ 700 ብር እንደሚከፍሉ አንስተዋል፡፡ መንገዱ 50 ኪሎ ሜትር የማይሞላ ቢኾንም ረጅም ጊዜ እንደሚጓዙ ነው የገለጹት፡፡
አሁን ላይ የመንገድ ሥራው ከተቋረጠ ሦሥት ዓመታት ኾኖታል፤ የችግሩን አሳሳቢነት በማየት የሚመለከተው አካል አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡
የመርሐቤቴ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ጌታው በላይግዛው የመንገድ ሥራው ከተጀመረ መቆየቱን እና እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ መንገድ ቆረጣ ሥራዎችን ጀምረው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና ተቆርጠው ማፋሰሻ ያልተሠራላቸው የመንገዱ ክፍሎች ውኃ በማቆር መንገዱን አስቸጋሪ አድርገውታል፤ በተለይ ዝናብ ወቅት አያንቀሳቅስም ነው ያሉት፡፡
በማኅበረሰቡ የየዕለት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯልም ብለዋል፡፡ ችግሩም በየደረጃው እየተነሳ እንደኾነ ገልጸዋል። መንገዱ በተቋራጩ የአቅም ውስንነት ሲጓተት ቆይቶ በኋላም በጸጥታው ችግር ምክንያት መቋረጡን አንስተዋል።
የመንገዱ አስቸጋሪነት ትርፍ አምራች እና የማዕድን ባለጸጋ የኾነውን መርሐቤቴ ወረዳን ለማልማት የሚመጡ ባለሀብቶችን አስቀርቶብናል ነው ያሉት፡፡
የመንገዱ መገንባት የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚፈጥር ከአጎራባች አካባቢዎች ጋር የሚያገናኝ ነው ብለዋል፡፡ መርሐቤቴን ለማሳደግ የመንገድ ጥያቄ የመጀመሪያው በመኾኑ የሚመለከተው አካል በአፋጣኝ መተግበር እንዳለበትም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የደብረ ብርሃን እና አካባቢው ፕሮጀክት አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ንጋቱ ውድነህ የኮኮብ መስክ-መርሐቤቴ (ዓለም ከተማ) መንገድ የመካጡሬ-ዓለም ከተማ ሁለተኛው ምዕራፍ መኾኑን ተናግረዋል።
ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞለት በቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በ2016 ዓ.ም እንዲጠናቀቅ ታስቦ ወደ ሥራ መገባቱንም አስታውሰዋል፡፡ መንገዱ 47 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው። አስፓልት ኮንክሪት ኾኖ ለመገንባት ነው ውል የተወሰደው ብለዋል፡፡
ኾኖም ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ የመሬት መንሸራተት፣ የካሳ ክፍያ መዘግየት፣ የተቋራጩ ደካማ አፈጻጸምን ጨምሮ ችግሮች እንዳጋጠሙ አንስተዋል፡፡
ችግሮቹን ለመፍታትም የዲዛይን ክለሳ እና የተቋራጩን አፈጻጸም እንዲሻሻል የመደገፍ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
በችግሮች ምክንያት ሲጓተት ቆይቶ አፈጻጸሙ 38 በመቶ ላይ እንዳለ መንገዶች ተቆርጠው ሳይስተካከሉ በአካባቢው በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከነሐሴ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ሥራው በጊዜያዊነት መቋረጡን ነው የተናገሩት። ከተቋራጩ ጋር የነበረው ውልም ተቋርጦ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተይዟል ብለዋል፡፡
መንገዱ አሁን አስቸጋሪ ኹኔታ ላይ በመኾኑ ማኅበረሰቡ በተደጋጋሚ መፍትሔ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን ያነሱት ሥራ አሥኪያጁ ለጊዜው መንገዱን ጠግኖ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በኮንትራክሮች የተነካካ እና የተበላሸ በመኾኑ በአንድ የጥገና ማዕከል ለማሠራት መቸገራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ክረምቱ ከመግባቱ በፊት በጊዜያዊነት እስከ ጀማ ወንዝ ድረስ ያለውን 20 ኪሎ ሜትር መንገድ በሀገር ውስጥ ተቋራጭ በሲሚንቶ ኮንክሪት እንዲሠራ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡
እስከ ዓለም ከተማ ያለውን መንገድ ለማስጠገንም በሂደት ላይ እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡ ዘላቂ የኾነውን ዋና የአስፋልት መንገድ ለማሠራት በቀጣይ በጀት ዓመት በሌላ ጨረታ ውል ተወስዶ እንደሚሠራ ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
