ባለሃብቶች ፈቃድ በወሰዱባቸው ማዕድናት እንዲያለሙ ድጋፍ ይደረጋል።

49
ባሕር ዳር: የካቲት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የከበሩ ማዕድናትን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናት ይገኛሉ። አይነት እና መጠኑ ቢለያይ እንጅ በኹሉም የክልሉ አካባቢዎች ማዕድናት እንደሚገኙም ይነገራል።
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደግሞ የማዕድን ሃብት ከሚገኙባቸው የክልሉ አካባቢዎች መካከል ናቸው። በእነዚህ አካባቢዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደረጉ የማዕድን አሰሳ ጥናቶች በርካታ ማዕድናት እንደሚገኙም ተረጋግጧል።
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የማዕድን ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ አበባው መኮንን በብሔረሰብ አሥተዳደሩ 21 ማዕድናት መኖራቸው በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተለይ የብረት ማዕድን ላይ የአሰሳ ጥናት መካሄዱን አንስተዋል። የማዕድኑን መጠን ለመለየትም ጥረት ተደርጓል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሁለት ባለሃብቶች የግራናይት ማዕድን ለማምረት፤ አንድ ባለሃብት ደግሞ ሲልካ ሳንድ ለማምረት ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል።
በብረት ማዕድን ፈቃድ ለማውጣት እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ባለሃብቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚፈልጉ ማዕድናትን ለማውጣት የመሠረተ ልማት እና የጸጥታ ችግር እንቅፋት እንደኾነባቸው ነው ያነሱት።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የማዕድን ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ታየች ዘለቀ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የማዕድናት አሰሳ ጥናት ላይ በሠፊው ተሠርቷል ብለዋል።
እስካሁንም 13 ማዕድናት እንዳሉ በጥናት ተረጋግጧል ነው ያሉት። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አዳዲስ ማዕድናት እየተገኙ እንደኾነም ጠቁመዋል።
የአሰሳ ጥናት ከማድረግ ባሻገር በክልሉ መንግሥት ድጋፍ ብረትን ጨምሮ ፋይዳ ያላቸውን ተጨማሪ ማዕድናት ለማምረት እየሠራን ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አበባ ጌታሁን በክልሉ 51 የሚኾኑ ማዕድናት እንደሚገኙ በጥናት ተረጋግጧል ነው ያሉት።
በ2018 በጀት ዓመት እስከ ሁለተኛ ሩብ ዓመት ድረስ የተለያዩ ማዕድናት በጥናት እየተለዩ ነው ብለዋል። ጥናቱ ሲቀጥል ቁጥሩም ሊጨምር እንደሚችል አመላክተዋል።
በክልሉ ብዙ ባለሃብቶች ፈቃድ ወስደው በርካታ ማዕድናት እያወጡ እና ገቢ እያስገኙ ቆይተዋል ነው ያሉት። ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ለክልሉ አዲስ የኾነው የከሰል ድንጋይ እየተመረተ መኾኑን ገልጸዋል።
የብረት ማዕድን በተገኘባቸው አካባቢዎች ወደ ሥራ ለመግባትም ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ ተከናውኖ ባለሃብቶች ለማልማት ጥያቄ እያቀረቡ ነው ብለዋል። ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ምርት ለመግባት ሂደት ላይ ያሉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በማዕድን ዘርፉ የመሠረተ ልማት እና የጸጥታ ችግሮች፤ ከመመሪያ ውጭ የኾኑ የካሳ እና የይገባኛል ጥያቄዎች ለባለሃብቶች እንቅፋት መኾናቸውን ተናግረዋል።
ቢሮው ችግሮችን ቀድሞ በመረዳት ከማኅበረሰቡ እና ከባለሃብቶች ጋር ውይይት በማድረግ ችግሮች እየተቀረፉ እና ባለሃብቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ግፊት እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
ባለሃብቶች በራሳቸው አቅም የመሠረተ ልማት ችግሮችን እየፈቱ ወደ ሥራ እንዲገቡ ያስፈልጋል ነው ያሉት። በርካታ ባለሃብቶችም ፈቃድ በወሰዱባቸው የማዕድናት ዘርፎች የመንገድ መሠረተ ልማት እየሠሩ ማዕድናትን ወደ ማውጣት ሥራ እየገቡ እንደሚገኙም ገልጸዋል። ይህም የራሳቸውን ችግር ከመፍታታቸው በተጨማሪ ለአካባቢው ማኅበረሰብም ድርብ ጠቀሜታ ያለው በመኾኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሃብቶች ፈቃድ በወሰዱባቸው ማዕድናት እንዲያለሙ እና ለገበያ እንዲያቀርቡ ቢሮው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአካባቢ ጸጥታን ለማስጠበቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
Next articleየብልጽግና ፓርቲ የማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት በአማራ ክልል ደረጃ ይፋ የማድረጊያ መድረክ እየተካሄደ ነው።