የአካባቢ ጸጥታን ለማስጠበቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

9
ወልድያ: የካቲት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳደር ከዞን መምሪያ እና ከጉባላፍቶ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር “ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነት ትፀናች” በሚል መሪ መልዕክት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መክሯል።
የምክክሩ ተሳታፊዎች የአካባቢውን የጸጥታ መደፍረስ የመንግሥት ሠራተኛው ላይ ሁለንተናዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል ብለዋል። በተለይም በደኅንነት ስጋት እና በኑሮ ውድነት ቀጥተኛ ተጎጅ ኾነናል ነው ያሉት።
ተሳታፊዎቹ ጫካ ያሉት ልጆች ሀገር አፍራሽ ወገኖች ጋር ያላቸውን ትብብር በማስቆም ሰላማዊ አማራጭ እንዲከተሉ የማድረግ ኀላፊነትን መወጣት ይገባልም ብለዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ወንድምነው ወዳይ ዞኑ ያማያልቅ ጸጋ፣ ታሪክ እና መልማት የሚችል መልካምድር ባለቤት ኾኖ እያለ ኅብረተሰቡ አካባቢውን እንዳያለማ ግን የውስጥ እና የውጭ ጥላቶቹ አቅደው እየሠሩ ነው ብለዋል።
የጠላት ቅንጅታዊ ሴራ እና ዓላማ የተለያየ ነው ያሉት አቶ ወንድምነው ችግሩን ተረድተን ከችግር ጠማቂነት ወጥተን ነገሮችን ለመጋፈጥ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ከድር ሙስጠፋ መጎዳትን ማቀንቀን እና የችግሩን አስከፊነት በመድረክ ማውራ ብቻ ለውጥ አያመጣም ይሁን እንጅ ዕውነትን ተጋፍጦ ለመፍተሄ መሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
እየተፈጠረ ላለው የጸጥታ ችግር ባለቤትነቱን ለመሪዎች ብቻ መተው አይገባም፤ ሁሉም ለብሔራዊ ጥቅም እና ለሉዓላዊነታችን መሥራት ይገባል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየታጠቁ ኃይሎች አዋጭ ወደ ኾነው የሰላም አማራጭ ሊመጡ ይገባል።