የታጠቁ ኃይሎች አዋጭ ወደ ኾነው የሰላም አማራጭ ሊመጡ ይገባል።

9
ደባርቅ: የካቲት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን ከተውጣጡ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም እና የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በደባርቅ ከተማ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት የቆየውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት በመቅረፍ እና የሀገርን ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ ብሔራዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሀገር ሉዓላዊነት እና በብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ጥቃት የሚወገዝ እና በየትኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።
ባለፉት ጊዜያት የተካሄዱ ጦርነቶች እና ግጭቶች እንደ ሀገር በርካታ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማድረሳቸውንም አንስተዋል።
ካለፈው መማር ያልቻሉ እና ተደጋጋሚ የጸብ አጫሪነት ተግባር የሚፈጽሙ የታጠቁ ኃይሎች ቆም ብለው በማሰብ አዋጭ ወደ ኾነው የሰላም አማራጭ ሊመጡ ይገባልም ነው ያሉት።
የሰሜን ጎንደር ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ዳኝነት ሙሉሰው መንግሥት የሰላም አማራጭን አስቀድሞ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር ሢሠራ ቆይቷል ብለዋል።
በዚህም በርካታ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። በቀጣይም ይሄ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።
ከግጭት የሚጠቀም ቡድንም ኾነ ግለሰብ ባለመኖሩ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ሁሉም ባለድርሻ አካል ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪ ዘላለም ልጃለም (ዶ.ር) ባለፉት ጊዜያት መንግሥት የሰላም አማራጭን አስቀድሞ ሢሠራ የቆየው የአማራ ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት እንዲያገኝ ባለው ጽኑ ፍላጎት ምክንያት ነው ብለዋል።
የሰላም አማራጭን ወደ ጎን በመተው በግጭት ጠማቂነት በሚሳተፉ ሕገ ወጥ ቡድኖች ላይ ሕግ የማስከበር እርምጃ ሲወስድ መቆየቱንም ገልጸዋል።
በቀጣይም የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሀገር ሰላም እና ለቀጣዩ ትውልድ ሕልውና ሲሉ ለሰላም በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
መንግሥት የሕዝብን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ለመፍታት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአፈጣጠር ችግር ላለባቸው ወገኖች የሕክምና ዘመቻ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ተካሂዷል።
Next articleየአካባቢ ጸጥታን ለማስጠበቅ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።