
ባሕር ዳር: የካቲት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ ጤና ቢሮ ከአጋር ድርጅቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በክልሉ የአፈጣጠር ችግር ያለባቸውን ወገኖች ለመደገፍ እና ማኅበረሰቡ እንዳያገላቸው ለማድረግ” የላቀ ተደራሽነት” በሚል መሪ መልዕክት የግንዛቤ ማስጨበጥ እና የሕክምና አገልግሎት የሚያካትት የማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂዷል።
መርሐ ግብሩ ወደ ተግባር ከመግባቱ በፊት በክልል ደረጃ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት አሳትፎ የአፈጣጠር ችግር ሕክምናን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ግልጽ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው።
በዚህም በችግሩ ዙሪያ ያለውን ዝቅተኛ ግንዛቤ ለማሻሻል እና በሕክምና ሊሰጡ የሚችሉ አገልግሎቶችን በተመለከተ የጤና ቢሮ የፕሮጀክት ሀረር አስተባባሪ ንጋቱ የሻንበል የመወያያ ጥናታዊ ጹሑፍ አቅርበው ከመድረክ ተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎበታል።
አስተባባሪው በቀጣይ የአፈጣጠር ችግር ላለባቸው ልጆች የሚሰጠውን የሕክምና ማዕከልም ይፋ አድርገዋል።
በዚህም፦
የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ ቀዶ ሕክምና ከአዲስ አበባ በሚመጡ ስፔሻሊስት ሐኪሞች ይሰጣል ነው ያሉት ።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አበበ ተምትሜ የአፈጣጠር ችግር በተለያዩ ምክንያቶች ይከሰታል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍም ክልሉ ሕጻናትን አድኖ የነገ ትውልድ ተረካቢ ለማድረግ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እና የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
በዚህም ከ2ሺህ 300 በላይ የቆልማማ እግር ችግር ያለባቸውን ሕጻናት የሕክምና ክትትል እንዲያደርጉ ተደርጓል ብለዋል።
የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸውን ሕጻናትንም ከስምንት ዓመታት በፊት ጀምሮ ሕክምና ሲደረግ መቆየቱንም ነው የተናገሩት።
በዚህም በአማካይ በዓመት ውስጥ 300 ለሚደርሱ ሕጻናት የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል ነው ያሉት።
“የአፈጣጠር ችግር የጤና ችግር ብቻ ሳይኾን ማኅበራዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ተጽዕኖ ያለው ጉዳይ ነው፤ ስለዚህ በተባባሪነት በመሥራት የተጎዱትን ወገኖች ወደ ሕክምና ማቅረብ እና ማኅበረሰቡ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት መቀየር ዋና ትኩረታችን ነው” ብለዋል።
ምክትል ኀላፊው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ፣ የሕክምና አገልግሎትን ማስፋፋት እና የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት ማሳደግ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።
የአፈጣጠር ችግር ሊታከም የሚችል ነው፤ ማንኛውም የተጎዳ ወገን ከማኅበረሰብ መገለል ይልቅ ወደ ሕክምና ተቋም መቅረብ አለበት ነው ያሉት።
የጤና ሚኒስቴር የስፔሻሊቲ እና ተሀድሶ አገልግሎት ዴስክ ኀላፊ ኤርሚያስ ሙላቱ እስከ የካቲት መጨረሻ ድረስ ባሉ ቀናቶች የአፈጣጠር ችግሮች ያለባቸው ልጆች ላይ የሚኖረውን የሕክምና ዘመቻ የግንዛቤ ፈጠራ በላቀ ተደራሽነት ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ወሩ ከዚህ ችግር ጋር የሚፈጠሩ ልጆችን በሕክምና ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ነው ብለዋል።
በእነዚህ ቀናቶች ውስጥ በተለያየ መልኩ ከአፈጣጠር ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን በየደረጃው የማከም እና የመከላከል ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።
በቀጣይ ይህንን ችግር ቀድሞ ለመከላከል አንዲት እናት ከእርግዝና በፊት ቅድመ ምርመራ በማድረግ እና በእርግዝና ወቅት በሚደረግ ምርመራ እና እንክብካቤ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ችግሩ ከተከሰተ በኋላም የልየታ ሥራ በመሥራት እና አጋዥ ቴክኒዎሎጅዎችን በመጠቀም ማከም እንደሚገባም ነው ያብራሩት።
ችግሩ ላለባቸው ልጆች ከሌላው ሰው በተለየ እነሱን ያማከለ እና ምቹ የኾነ አካባቢን መፍጠር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
አቶ ኤርሚያስ የአፈጣጠር ችግር በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት የሚጠይቅ መኾኑን ገልጸው ይህ ጉዳይ በጤና ተቋማት ውስጥ ብቻ የሚፈታ አይደለም፤ የማኅበረሰብ አመለካከት ለውጥ እና የተቀናጀ ድጋፍ ይፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም መንግሥት የአፈጣጠር ችግር ሕክምናን በሁሉም ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ የ10 ዓመታት ሮድ ማፕ በመቅረጽ በሰው ኀይል ሥልጠና፣ በመሳሪያ አቅርቦት እና በተቋማት ማጠናከር ላይ እየሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም እስከ የካቲት 24/2018 ዓ.ም በአማራ ክልል የአፈጣጠር ችግር ያለባቸውን ልጆች የማከም ዘመቻ ይካሄዳል ነው ያሉት።
ይህንን ዘመቻ ተደራሽ ለማድረግ አጋር አካላት፣ የሚመለከታቸው ተቋማት እና የሚዲያ አካላት በጋራ በመኾን እና በመደጋገፍ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ:-ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
