
ባሕር ዳር: የካቲት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወር ዕቅድ አፈጻጸሙን እየገመገሙ ነው።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በበጀት ዓመቱ በክልሉ አሻጋሪ ዕቅድ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ አምራች ኢንዱስትሪው ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ 609 ቢሊዮን ብር በላይ መዋዕለ ነዋይ ወደ ክልሉ ለማምጣት ታቅዶ ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። ባለፉት ስድስት ወራት በተቋሙ የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል ነው ያሉት።
በአምራች ኢንዱስትሪዎች፣ በማዕድን፣ በአገልግሎት፣ በዘመናዊ ግብርና እና በቱሪዝም የተሻሉ አልሚዎችን ለማምጣት ታቅዶ ተሠርቷል ብለዋል።
በዚህም 183 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 1 ሺህ 867 አዳዲስ አልሚ ባለሀብቶችን መቀበላቸውን ገልጸዋል። ምንም እንኳን ችግሮች ቢኖሩም በክልሉ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መኾኑን ነው የተናገሩት።
በስድስት ወራት 85 አምራች ኢንዱስትሪዎች እና 280 ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ወደ ምርት ገብተዋል ነው ያሉት።
በመሬት አቅርቦት በኩል የነበሩ ችግሮችን ከመሬት ቢሮ ጋር በመፍታት ለ177 አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ለ122 ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች 4 ሺህ 126 ሄክታር መሬት ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ የሚገቡ ከ321 ቶን በላይ ተኪ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማምረት ከ366 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬን ማዳን ተችሏል ነው ያሉት። 43ሺህ ቶን የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ 112 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንደተገኘም ገልጸዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 62 ነጥብ 4 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል።
ከ47 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን እና የዘርፉን አገልግሎት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ እንደኾነም አንስተዋል። ወደፊትም ችግሮችን መፍታት እና ተቋማዊ ቅንጅት ላይ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
