ያለ ሰላም ትምህርትን፤ ያለ ትምህርትም ዘላቂ ሰላምን ማምጣት አስቸጋሪ ነው።

6
ደሴ: የካቲት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከወሎ ቀጣና የዞን እና የወረዳ ትምህርት መሪዎች፣ ከ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህራን፣ ሱፐር ቫይዘሮች እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር የ2018 ዓ.ም የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን በደሴ ከተማ እየገመገመ ነው።
የክልሉ መንግሥት የትምህርት ዘርፉን ለማሻሻል ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ የመደበኛ እና ካፒታል በጀት መድቦ እየሠራ ነው ተብሏል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ የትምህርት ቤት ምገባን ስኬታማ ለማድረግ ኅብረተሰቡ እያደረገ ያለው ርብርብ አበረታች መኾኑን ገልጸዋል።
ለዚሁ አገልግሎት 500 ሚሊዮን ብር ተመድቦ የግብዓት ግዥ እየተፈፀመ ይገኛልም ነው ያሉት።
በክልሉ ሦሥት አዳሪ ትምህርት ቤቶች እና አራት ሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ግንባታቸው እየተፋጠነ መኾኑን ገልጸዋል።
ለቀጣይ ዓመት የመማር ማስተማር ሥራ ለማድረስ ክትትል እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል።
የ2018 በጀት ዓመት በሁሉም መደበኛ ተግባራት የተማሪ ተሳትፎን ጨምሮ ካለፉት ሁለት ዓመታት የተሻለ እና ተስፋ የሚሰጥ ነው፤ ነገር ግን በክልሉ ውስጥ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት አሁንም ድረስ ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎች በርካታ ናቸው ነው ያሉት።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮነን ዞኑ በጸጥታ ችግር ቢፈተንም የትምህርትን ተደራሽነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው ብለዋል። በጸጥታ ችግሩ አሁንም በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ሰላም እና ትምህርት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው ያሉት አሥተዳዳሪው “ያለ ሰላም ትምህርትን፤ ያለ ትምህርትም ዘላቂ ሰላምን ማምጣት የሚታሰብ አይደለም” ብለዋል።
ተማሪዎች እና መምህራን ያለ ስጋት የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እና መሠረተ ልማቶች እንዲጠበቁ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።
ትምህርት እና ሰላም ሲጣመሩ የበለጸገ ትውልድ ለመፍጠር ጉልህ ሚና ስላለው ሰላምን ለማጽናት ሁላችንም መተጋገዝ ይገባናል ብለዋል።
በግምገማው ያለፉት ስድስት ወራት የዞኖች፣ የወረዳዎች እና የከተማ አሥተዳደሮች የትምህርት አፈጻጸም ላይ ውይይት በማድረግ ለቀጣይ ስድስት ወራት የአሠራር አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ:-ሳሙኤል ኪሮስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሥራ ስምሪት የዜጎችን ደኅንነት ያረጋገጠ እንዲኾን እየተሠራ ነው።
Next articleመግባባት የተሳነው ትውልድ ሀገራዊ ነጻነቱን እና ደኅንነቱን ማስጠበቅ አይችልም።