
ገንዳ ውኃ: የካቲት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ክፍት የሥራ ዘርፎች ወጣቶችን ለማገናኘት የሚረዳ የባዮሜትሪክ ኪት ማሽን የሥራ ማስጀመሪያ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ሥራ እና ክህሎት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ቢያዝን አያና መምሪያው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ከ24ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል ነው ያሉት።
ሥልጠናውም የዞኑን ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ወደ ኢትዮጵያ የሥራ ገቢያ መረጃ ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ እና እንዲመዘገቡ ለማድረግ መኾኑን አብራርተዋል።
በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ክፍት የሥራ ዘርፎች ወጣቶችን ለማገናኘት የሚረዳ የሥራ ማስጀመሪያ ሥልጠና እንደኾነም ተናግረዋል።
አጠቃላይ ከ2ሺህ 400 በላይ ወጣቶችን የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የኦላይን ምዝገባ ሥራውን ለማስጀመርም ከተለያዩ ከተማ እና ወረዳ ለመጡ ለኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ሥልጠናው እየተሰጠ ነው ብለዋል።
በዚህም የክልሉ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ 14 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ ሰባት ማሽኖች እንዲገዙ አድርጓል። አራቱ ማሽን ወደ ዞኑ መግባታቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ የተለያዩ ቦታዎች ማሽኖች አገልግሎት እንደሚጀምሩም ተጠቁሟል።
የፌዴራል ሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የአማራ ክልል የሥልጠና አስተባባሪ ሳምሶን የኔሰው የዜጎችን መብት፣ ደኅንነት እና ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የሀገር ውስጥም ኾነ የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው።
ሥልጠናው ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መኾኑም ተጠቁሟል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
