“ሴፍቲኔት የድሆች እንባ አባሽ ነው” የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች

10
ደብረ ብርሃን: የካቲት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ​የደብረ ብርሃን ከተማ ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የሁለተኛ ዙር ተጨማሪ በጀት የምግብ ዋስትና ሴፍቲኔት ፕሮጀክት የአካባቢ ልማት ተጠቃሚዎችን አስመርቋል።
ፕሮግራሙ ዜጎች ከቤታቸው ወጥተው ተጨማሪ ገቢ እንዲያመነጩ እና በዘላቂነት እንዲደራጁ በማድረግ ረገድ ትልቅ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
​የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ከ37 ሺህ 400 በላይ ዜጎችን በሴፍትኔት ፕሮግራም በማደራጀት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ይህም ዜጎችን ከመጥቀም ባለፈ ከተማዋን ጽዱ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል ነው ያሉት።
የከተማ አሥተዳደሩ የምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግርማ ድባቤ ከተማዋን ምቹ ከማድረግ ጎን ለጎን የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የተሠራው ሥራ ለሌሎች አርዓያ የሚኾን ተሞክሮ የተቀመረበት እንደነበር ተናግረዋል።
​የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት አሥተባባሪ ሀሠን ሙህዬ የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል እና በዘላቂነት ተጠቃሚ ማድረግ የክልሉ ዋና የትኩረት አቅጣጫ መኾኑን ገልጸዋል። የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተጠቃሚዎችን ከመመልመል ጀምሮ በኑሮ ደረጃቸው እንዲሻሻሉ በማድረግ ረገድ ስኬታማ መኾኑን ተናግረዋል።
​የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የኾኑት ወይዘሮ ፀዳለች አለማየሁ ለአሚኮ እንደተናገሩት “ሴፍትኔት የድሆች እንባ አባሽ ነው፤ ሠርቶ መለወጥ እንደሚቻል አሳይቶኛል” ብለዋል። ጠንክሮ ከሠሩ መለወጥ እንደሚቻል ፕሮግራሙ እንዳስተማራቸው የገለጹት ወይዘሮ ፀዳለች በቀጣይም አሁን ካላቸው የተሻለ ኑሮ ለመኖር ተግተው እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
​ሌላኛው ተጠቃሚ አቶ ደምሰው ወርቅነህ ከተረጅነት ወደ ሌሎች ረጂነት ያሸጋገረኝ ሴፍትኔት የምኮራበት ተግባር ነው ብለዋል።
ፕሮግራሙ ሠርቶ መለወጥን እንዳሳያቸው የገለጹት አቶ ደምሰው ዕድሉን ላመቻቹ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ብርቱካን ማሞ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ተጠናቀቀ።