
ባሕር ዳር: የካቲት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከየካቲት 05 እስከ 08 /2018 ዓ.ም ሲያካሂድ የቆየውን 4ኛው “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” መዝጊያ መርሐ ግብር አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል ።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባሕር ዳር ከተማን ውብ፣ ጽዱ እና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የጣና ዳር ልማት እና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ጠቅሰዋል።
የተሠሩ የልማት ተግባራት በከተማዋ ቱሪዝምን ከማስፋት ባለፈ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትኾን ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል። በከተማዋ የሚገኙ አምራቾችም በከተማዋ በተሠሩ የጣና ዳርቻዎች ላይ ወጥተው ምርት እና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት።
በከተማ አሥተዳደሩ በኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ የከተማ አሥተዳደሩ የመሬት ችግርን ለመፍታት 122 ሄክታር መሬት ከሦስተኛ ወገን ነጻ ለማድረግ የካሳ ግምት ተሠርቶ መጽደቁንም ተናግረዋል።
በአጭር ጊዜ ለባለሃብቶች የማስተላለፍ ሥራ የሚሠራ ይኾናል።
ከዚህም ባለፈ የኢንዱስትሪ መንደርን ለማስፋት 13 ቀበሌዎች ወደ ከተማ አሥተዳደሩ በመካተታቸው የቦታ ልየታ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ባለሀብቶች በተሟላ መንገድ ገብተው እንዲያለሙ ማኅበረሰቡ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ እንዲሠራም አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” መርሐ ግብር የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬ ችግርን ለመፍታት አላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት የተዘጋጁት መርሐ ግብሮችም ኢንተርፕራይዞችን የሚያበረታታ መኾኑን ገልጸዋል። አምራቾች እርስ በእርሳቸው እና ከሸማቹ ማኅበረሰብ ጋር እንዲተዋወቁ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል። አምራቾች ያሉባቸውን ችግሮች ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በቅርበት ተገናኝተው እንዲነጋገሩ እና እንዲፈቱ ማስቻሉን ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
