
ባሕር ዳር፡ የካቲት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አጼ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ተብለው የነገሡት በዚህ ሳምንት በየካቲት አምስት ቀን ነበር፡፡
ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ስለ ንግሥናቸው ሲጽፉ የዚያኔው ደጅ አዝማች ካሳ በየካቲት 05/1847 ዓ.ም ደጅ አዝማች ውቤ እነግሥባታለሁ ብለው ባሠሯት እና ባስጌጧት በደረስጌ ማርያም እጨጌው በግራ ጳጳሱ በቀኝ ተቀምጠው መጸሐፈ ተክሊል እየተነበበ በአቡነ ሰላማ እጅ ሥርዓተ መንግሥት ተደርሶላቸው በመቀባት ቴዎድሮስ በተባለው ስመ መንግሥታቸው ነገሡ፡፡
ሲነግሡ የ35 ወይም የ36 ዓመት ጎልማሳ ናቸው፡፡ በዚሁ ቀን ባለቤታቸው ተዋበች አብረው ቆርበው ለእርሳቸው አክሊል ተደርጎላቸው እቴጌ ኾኑ ሲሉ ጽፈዋል፡፡
ብልኋ ሴት እቴጌ ጣይቱ ብጡል እረፍታቸው የካቲት 04/1910 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ነበር፡፡ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ከባለቤታቸው ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ ጎን በመቆም በንጉሠ ነገሥቱ ላይ የተጀመሩ የአውሮፓ ቅኝ ገዢ ሴራዎችን እና ጦርነቶችን የተቃወሙ ጀግና ሴት ናቸው። በዓድዋ ጦርነት ከነበሩ የጦር አዛዦችም አንዷ ነበሩ።
እቴጌ ጣይቱ ብጡል ከባለቤታቸው ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ ጎን በመኾን ኢትዮጵያን ለ24 ዓመታት ያሥተዳደሩ ጀግና ሴትም ነበሩ። የጣልያን ቅኝ ገዥ ኃይሎችን በመዋጋት እና በነበራቸው የፖለቲካ ተሳትፎም ይታወሳሉ። እቴጌዋ የኢትዮጵያን መዲና አዲስ አበባ ብለው የሰየሙም ናቸው።
የጣይቱ ብጡል እና የአጼ ምኒልክ ጋብቻ ጠንካራ የፖለቲካ ጥምረት ፈጥሯል። እቴጌ ተብለው ሲሰየሙ ከተለያዩ የአካባቢው ገዢዎች ጋር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጥምረት እንዲፈጠር አልያም በወታደራዊ አቅም የበለጠ ግዛታቸው እንዲጠነክር ከፍተኛ ሚናም ተጫውተዋል።
ጣይቱ ከምኒልክ እኩል ውሳኔዎችን ይወስኑ እና በሳል አመራር ይሰጡ እንደነበር ይነገራል። ዳግማዊ አጼ ምኒልክ በ1909 ዓ.ም ክፉኛ ሲታመሙ እቴጌ ጣይቱ አብዛኛውን ሀገሪቱን የመምራት ሚናም ተጫውተዋል። ምንጭ፦አጼ ምኒልክ በጳውሎስ ኞኞ
እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1918 በደቡብ አፍሪካ ምሥራቃዊ ኬፕ የተወለዱት ማንዴላ በደቡብ አፍሪካ በጥቁሮች ላይ የዘር መድሎ የሚያስፈጽመውን የአፓርታይድ ሕግ በመቃወም የኤንሲን ሰላማዊ ተቃውሞ መርተዋል።
በደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ ማዲባ እየተባሉ የሚጠሩት ኔልሰን ማንዴላ በግዳጅ የሚፈናቀሉትን ደቡብ አፍሪካውያን ጥቁሮችን፣ ነጻ እንቅስቃሴያቸውን የሚገድቡ እና መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶቻቸውን ለመንፈግ “ሕግ አውጥተዋል” ያሉትን ሁሉንም ለመከላከል ነው የታገሉት። በዚህም ትግላቸው የሕይዎት አጋማሻቸውን በእስር እንዲያሳልፉ ኾነዋል።
ዕለቱ የካቲት 04/1990 የደቡብ አፍሪካ ነጻ አውጭ ኔልሰን ማንዴላ 27 ዓመታትን በእስር ቤት ካሳለፉ በኋላ ከቪክቶር ቨርስተር እስር ቤት ከወቅቱ ባለቤታቸው ዊኒ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ከእስር ሲወጡ ደቡብ አፍሪካውያን በደስታ እንባ ተራጭተዋል። ምንጭ፦ ረጅም ጉዞ ለነጻነት መጽሐፍ (Long Walk to Freedom)
በምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
