የፍትሕ ምንጩ ዙፋን ዋልዋጅ!

31

ባሕር ዳር፡ የካቲት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ግጭት እና አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ በርካታ ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓቶች አሉ።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ማኅበረሰብ ለዘመናት ሲገለገልበት የቆየው እና አሁንም እየተገለገለበት የሚገኘው ዙፋን ዋልዋጅ የእርቅ እና ሽምግልና ሥርዓት ደግሞ አንዱ ነው።

በዙፋን ዋልዋጅ የእርቅ እና ሽምግልና ሥርዓት ተጠቃሚ የኾኑት የአርማጭሆ አካባቢ ነዋሪው አስጠራው ኹነኛው በውርስ ሊያገኙት የሚገባን የአባታቸው መሬት በቅርብ ዘመዳቸው ተወስዶ እንደነበር ነግረውናል። ጉዳዩ ወደ ዙፋን ዋልዋጅ ከመሄዱ በፊት በመደበኛ ፍርድ ቤት ታይቶ እንደነበርም አስታውሰዋል።

በሀሰተኛ መረጃዎች ምክንያትም የአባታቸው ውርስ አይገባህም ተብለው እንደነበር ነው የጠቀሱልን። ይህን ተከትሎ በተፈጠረ ግጭትም የመጠፋፋት እሳቤ እንደነበር አስታውሰዋል። ይህን የሰሙ የዙፋን ዋልዋጅ አስታራቂዎች ጉዳዩን ይዘው በሁለቱም ወገን ታማኝ አስረጅዎችን ተመልክተው በባሕላዊ የእርቅ እና ሽምግልና ሥርዓት ውሳኔ ሰጠው እንዳስማሟቸው ነው የገለጹልን።

ስምምነቱ እውነት ላይ የተመሠረተ፣ አድሎ የሌለበት፣ ከልብ ይቅር ባይ በመኾን የተመሠረተ፣ አለመግባባት ወደ ፍቅር የተለወጠበት ነበር ሲሉ አጫውተውናል።

በዙፋን ዋልዋጅ የእርቅ እና ሽምግልና ሥርዓት ያለምንም ክፍያ፣ ቀጠሮ እና መጉላላት በአጭር ጊዜ ፍትሕ እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል። የጉልበት ኪሳራ እና የገንዘብ ወጭም እንደቀነሰላቸውም ነግረውናል።

የዙፋን ዋልዋጅ ባሕላዊ የእርቅ እና ሽምግልና ሥርዓት አባል የኾኑት እንዳልክ ኹነኛው ደግሞ ዙፋን ዋልዋጅ የቆየ እና ከቅድመ አያቶቻቸው ጀምሮ የነበረ ባሕላዊ  የዳኝነት ሥርዓት መኾኑን ነግረውናል። የአስታራቂ ማኅበሩ አባላትም በዋናነት ተሰሚነት ያላቸው፤ በማኅበረሰቡ የተመረጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር  ሽማግሌዎች እና ባሕሉን የሚያውቁ ምሁራን የተካተቱበት እንደኾነ ነው የገለጹልን።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ወጣቶች እና ሴቶች በተለያየ ሁኔታ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየተደረገ መኾኑንም ነግረውናል።

ዙፋን ዋልዋጅ ባሕላዊ የእርቅ እና ሽምግልና ሥርዓት ስያሜውን ያገኘው በ16ኛው ክፍለ ዘመን የአጼ ሱስንዮስ የልጅ ልጅ አድያም ሰገድ በማዕከላዊ አርማጭሆ ወረዳ ለአንድ ቀበሌ የሰጧትን ስም መነሻ አድርጎ ነው ብለዋል።


ቦታው በተራራ ላይ ያለ ደልዳላ መሬት ስለኾነ የዙፋን ማስቀመጫ ይመስላል ባሉት ሃሳብ መነሻነት ዙፋን ዋልዋጅ ተብሏል ነው ያሉት። ይህም በአቅራቢያ ባለ ቤተክርስቲያን ውስጥ በሚገኝ መንፈሳዊ የስንክሳር መጽሐፍ ሰፍሮ እንደሚገኝ ጠቅሰውልናል። የአጼ ሱስንዮስ የልጅ ልጅ አድያም ሰገድም በዚሁ ባሕላዊ የፍርድ ሥርዓት በቦታው ፍርድ ይሠጡ እንደነበርም ይነገራል ነው ያሉት።

ሥርዓቱ ልክ እንደ መደበኛ ፍርድ ቤት ይግባኝን ጨምሮ ልዩ ልዩ የፍርድ ሥርዓቶችን እንደሚከተል ነው ያነሱት። እርስ በርስ የመገዳደል፤ ደም የመመላለስ ተግባር፤ እገታ፣ የጥቅም ይገባኛል ጉዳዮችን እና የጋብቻ ሁኔታን የሚዳኝ ሥርዓት ያለው ነውም ብለዋል።

የተበደለ የሚካስበት ሥርዓትም አለው ነው ያሉት። የእርቅ እና ሽምግልና ሥርዓቱ በቀደመው ዘመን የገዳይ እና የሟች ወገን ደም ይብቃ ብለው ይታርቁበት የነበረ እና አሁንም ያለ ከ500 ዓመታት በላይ ያሰቆጠረ “ደም በቃ” የሚባል ዛፍ ሥር በብዛት ይከወናል ነው ያሉት።

ዙፋን ዋልዋጅ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጥናት ከለያቸው 15 የሽምግልና ሥርዓቶች አንዱ ኾኖ መመረጡ ደግሞ ደስተኛ እንዳደረጋቸው ነግረውናል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የማዕከላዊ አርማጭሆ ወረዳ የባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገዛኸኝ ታከለ በቂ ባይኾንም እንደ ጽሕፈት ቤት ዙፋን ዋልዋጅ የእርቅ እና ሽምግልና ሥርዓትን የሚያስተዋውቁ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ባሕላዊ የእርቅ እና ሽምግልና ሥርዓቱ ብዙ ጥናት እንዳልተደረገበትም ጠቅሰዋል። ቀጣይ ሰፊ ጥናት እንዲደረግበት ደግሞ እንቅስቃሴ እየተደረገ መኾኑን ነው የገለጹት።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የባሕል ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይማም ሰይድ ደግሞ በአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም አዋጅ ቁጥር 298/2017 ዓ.ም መቋቋሙን ተናግረዋል። አዋጁ የትኛውም አካል በባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ጣልቃ እንዳይገባ እና ጥበቃ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

የአዋጁን መውጣት ተከትሎም በክልሉ ካሉ በርካታ የባሕል ፍርድ ቤቶች መካከል ሰብዓዊ መብትን የሚያከብሩ ሥርዓቶች ተለይተዋል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ሕገ መንግሥቱን የማይቃረኑ እና የማኅበረሰቡን ወግ እና ልምድ አክብረው አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያገለግሉ የእርቅ እና ሽምግልና ሥርዓቶች መካከል 15ቱ ተለይተው ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸውልናል። በእነዚህም ላይ ጥናት መደረጉን ነው የጠቀሱት።

አሁን ላይ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጥናት የተለዩ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች በክልሉ መንግሥት እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክትትል እና እገዛ እየተደረገ የጎደላቸውን የመሙላት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል።

በባሕላዊ ፍርድ ቤቶች በኩል የመንግሥት አሥፈጻሚ አካል እንዲኖር ጥያቄዎች ሥለነበሩ አሁን ላይ ምላሽ በሚሰጥ አግባብ የወረዳ ፍርድ ቤቶች የባሕል ፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ወስደው ያስፈጽማሉ ነው ያሉት።

በሥልጠና እና በቁሳቁስ የመደገፍ ሥራም መጀመሩን አንስተዋል። ዘመን እየተሻገሩ ለትውልድ እንዲተላለፉ ፣ ጥናታዊ ጽሑፍ ለሚሠሩ አጥኝዎች እና መረጃ ፈላጊዎችን ማገዝ እንዲችሉ፣ ለቀጣይ የሕግ ማሻሻያ ሥራዎችም ከፍተኛ አበርክቶ እንዲኖራቸው ማዕከሎችን ለመገንባት ዝግጅት መደረጉም ነው የገለጹልን።

ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓቶች የክልሉን የፍትሕ ሥርዓት ችግር ያቃልላሉ፤ የማኅበራዊ ግንኙነት መሻከር እንዲቀንስም ያግዛሉ ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጉባኤው ኢትዮጵያ ትላልቅ ዓለም አቀፍ መድረኮችን በስኬት ማስተናገድ እንደምትችል ያሳየችበት ነው።
Next articleየሀገር ፍቅር ተምሳሌት መሪ