ጉባኤው ኢትዮጵያ ትላልቅ ዓለም አቀፍ መድረኮችን በስኬት ማስተናገድ እንደምትችል ያሳየችበት ነው።

4

አዲስ አበባ፡ የካቲት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እየተካሄደ ነው። የጉባኤውን ሂደት አስመልክተው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ድኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ መግለጫ ሰጥተዋል።

ጉባኤው “ዘላቂ የውኃ አቅርቦት እና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፥ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ መልእክት እየተካሄደ መኾኑን ሚኒስትር ድኤታው ገልጸዋል።

በትላንትናው ዕለትም የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባኤ መካሄዱን ገልጸው ጉባኤው በሰው ኃይል ልማት፣ በጤና፣ በትምህርት እና ሥልጠና፣ በኃይል ልማት፣ በግብር እና ተያያዥ ጉዳዮች የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እና የአፍሪካ መሪዎች በአዲስ አበባ ውጤታማ ጉባኤ ማካሄዳቸዉን ተናግረዋል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ድኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በመግለጫቸው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በቂ ዝግጅት ከተደረገበት በኃላ በዛሬው ዕለት መጀመሩን ጠቅሰዋል።

በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ጥቅሞቿን የሚያስጠብቁ እና በትብብር አብሮ ለመሥራት ያላትን አቋም አስመልክተው መልእክቶችን ማስተላለፋቸውን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊየን በላይ በላይ ሕዝብ ያላት ግን የባሕር በር አልባ መሆኗን አንስተዋል። በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን ለማሳካት ጥረቷን እንደምትቀጥል መናገራቸውንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

ሀገሪቱ ያላትን የውኃ ሃብት በትብበር በማልማት ቀጣናዊ የልማት ትስስርን ለመፍጠር እየሠራች መኾኗን በመግለጫቸዉ አንስተዋል።

በስንዴ ልማት በተገኘው ተጨባጭ ውጤት ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጧን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውም በመግለጫው ተጠቁሟል።

ኢትዮጵያ በጉባኤው የተናጠል እና የሁለትዮሽ ውይይቶችን እያካሄደች ትገኛለችም ብለዋል።
በአጠቃላይ ተገቢው ዝግጅት የተደረገበት እና ኢትዮጵያ ታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮችን በስኬት ማስተናገድ እንደምትችል የተረጋገጠበት ጉባኤ መኾኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ድኤታው ተስፋሁን ጎበዛይ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ኢብራሒም መሐመድ

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አፍሪካውያን የውኃ ሃብታችንን በትብብር መጠቀም አስፈላጊ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)