
አዲስ አበባ፡ የካቲት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
ጉባኤው እየተካሄደ ያለው ”ዘላቂ የውኃ አቅርቦት እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ መልዕክት ነው።
በጉባኤው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አፍሪካውያን የውኃ ሃብት የዕድገት መሠረት መኾኑን በመረዳት በትብብር መጠቀም አለብን ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዳግማዊ የዓድዋ ድል ምልክት በኾነው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ በሠራችው ሥራ ተጨባጭ ውጤት አምጥታለች ብለዋል።
በዚህም አፍሪካውያን የውኃ ሃብትን በአግባቡ መጠቀም ከቻልን በአፍሪካ ዕድገት ከፍ ያለ ተፅዕኖ ማሳደር እንችላለን ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት መጨረሻ 10 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ እየሠራች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ እና የዜጎችን ሕይዎት ለመቀየር በከተማ ብሎም በገጠር ሰው ተኮር ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሠራችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ከመከላከል አንጻር ትልቅ ሚና እየተወጣች መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
በኮፕ 32 ጉባኤ ላይ አፍሪካ በአንድ ድምጽ የመፍትሔ ሃሳቦችን ለዓለም ታቀርባለች ነው ያሉት፡፡
ዜጎችን የልማቱ ማዕከል ያደረገ የዲጂታል መሠረተ ልማት እየተገነባ መኾኑን ጠቅሰው በተለይም ፋይዳ የተሰኘው ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ከክፍያ ሥርዓቶች እና ከመረጃ ልውውጥ አውታሮች ጋር በመቀናጀቱ ዜጎች ቀልጣፋ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ መኾኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2020 በአፍሪካ ቀዳሚ የኾነውን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ማቋቋሟንም አስታውሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ በመደመር ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት ዝግጅት ላይ መኾኗን ገልጸዋል።
ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግር የአገልግሎት አሰጣጥን ከማዘመን ባለፈ የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠን አፍሪካ በዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ መድረክ ያላትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም መሃመድ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
