
ባሕር ዳር: የካቲት 7/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ጉባኤ በኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ተጀምሯል። በጉባኤው ላይ የተገኙት የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ አፍሪካ የዓለም የታሪክ መድረክ ዋና ተዋናይ እየኾነች መምጣቷን ጠቁመዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ገለጻ ጣሊያንም ኾነች አውሮፓ ያለ አፍሪካ ንቁ ተሳትፎ የወደፊት ብሩህ ተስፋ ሊኖራቸው አይችልም።
አሕጉሪቱ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት እና የእርሻ መሬት ብቻ ሳይኾን ወሳኙን የሰው ኃይል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ አሳስበዋል።
ጣሊያን በአውሮፓ እና በአፍሪካ መካከል እንደ ድልድይ ኾና ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሯ በተለይም ወጣቶች በቴክኖሎጂ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እንዲሰለጥኑ በትኩረት እየተሰራ መኾኑን ተናግረዋል።
ወጣቶች በስደት ምክንያት ሀገራቸውን ሲለቁ የታሪክ እና የባሕል ክፍተት እንደሚፈጠር በማንሳት ስደትን እንደ ብቸኛ አማራጭ ማየት “ራስ ወዳድነት” መኾኑን የካርዲናል ሮበርት ሳራህን ንግግር በመጥቀስ አስገንዝበዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ጥራት ያለው ትምህርት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ጠንካራ የኢንዱስትሪ ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የአፍሪካን ተሰጥኦ ወደ ውጭ ከመውሰድ ይልቅ በአሕጉሪቱ ውስጥ እንዲያድግ የሚያደርግ አዲስ የልማት ሞዴል እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርበዋል።
“ሁልጊዜም ከአፍሪካ አዲስ ነገር ይገኛል” የሚለውን የጣሊያናውያንን አባባል በመጥቀስ፣ የማይቻለውን ነገር በትብብር ወደ እውነት ለመለወጥ እና ዓለምን ለማስደመም ቃል እንገባለን ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
