“አፍሪካ የጋራ ዕቅዶቿን እንድታሳካ ቅድሚያ ለሰላም መሥራት አለባት” ፕሬዝዳንት ማኑኤል ጎንካልቬስ ሎሬንዞ

7

አዲስ አበባ፡ የካቲት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተጀምሯል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐመድ አሊ ዩሱፍ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና ሌሎች እንግዶች የተለያዩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

ጉባኤው የሚካሄደው ”ዘላቂ የውኃ አቅርቦት እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ መልዕክት ነው።

በጉባኤው ላይ የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር እና የአንጎላ ፕሬዝዳንት ማኑኤል ጎንካልቬስ ሎሬንዞ አፍሪካ የጋራ ዕቅዶቿን እንድታሳካ ቅድሚያ ለሰላም መሥራት አለባት ብለዋል።

አፍሪካ የጋራ እቅዶቿን እንድታሳካ ልንሠራ ይገባል ያሉት ሊቀመንበሩ በአፍሪካውያን አባቶች የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት ጠንካራ ትብብር ላይ ማተኮር እንደሚገባ አስረድተዋል።

የአፍሪካን ልማት እና ብልጽግና ለማረጋገጥ መሠረተ ልማትን ማሳደግ እና በሀገራት መካከል የመሠረተ ልማት መገንባት ይገባል ለዚህ ትልቁ እና ዋናው መሠረት ሰላም ነው ብለዋል።

አፍሪካ የሰው ኀይሏ የልማት መሠረቷ መኾኑን ማመን እንዳለባትም አስገንዝበዋል። ደንበር የማይገድበው የአባል ሀገራት ትብበር እና ባለብዙ ዘርፍ ዲፕሎማሲንም ማጠናከር የአፍሪካን መዳረሻ መደላድል ለመፍጠር ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል።

ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቡሩንዲ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበርነትን ተረከበች።
Next article“ሁልጊዜም ከአፍሪካ አዲስ ነገር ይገኛል” ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ