
ባሕር ዳር: የካቲት 7/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ በኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ተጀምሯል።
በኅብረቱ መደበኛ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)*ኢትዮጵያ የዜጎችን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገ የዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታን እና አሕጉራዊ ትስስርን ለማጠናከር ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን እየወሰደች መኾኑን አንስተዋል።
ይህም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዕቅድ አማካኝነት የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ ሽግግር ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ነው የተናገሩት።
በዕቅዱ ስር የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ዜጎች አገልግሎቶችን በቀላሉ የሚያገኙበትን ምህዳር ለመፍጠር ያለሙ ናቸው ተብሏል።
በተለይም የ”ፋይዳ” ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን ከዘመናዊ የክፍያ ሥርዓቶች እና ከብሔራዊ የመረጃ ልውውጥ መድረክ ጋር በማገናኘት ደህንነቱ የተጠበቀና ቀልጣፋ የንግድ ግብይት እንዲኖር እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ይህ አሰራር በዜጎች እና በኩባንያዎች መካከል አመኔታን በመገንባት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ያነቃቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት ዝግጅቷን ማጠናቀቋንም ይፋ አድርገዋል።
በመሠረተ ልማት ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰዎችን እና ገበያዎችን በማገናኘት ረገድ ግንባር ቀደም ሚናውን እየተወጣ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
ይህንን ስኬት አሕጉራዊ መሠረት ለማስያዝ አፍሪካን ከዓለም አቀፍ የንግድ ሰንሰለት ጋር የሚያስተሳስር ግዙፍና ዘመናዊ አውሮፕላን ማረፊያ በመገንባት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በስትራቴጂካዊ አጋርነት በመታገዝ በአፍሪካ ያለውን የዲጂታል ልዩነት ለመሙላት አገልግሎቱን ወደ ተለያዩ የአህጉሪቱ ሀገራት እያሰፋ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
