“ሀገር ያለ ሕዝብ እና መንግሥት፤ መንግሥት ደግሞ ያለግብር ሊቆሙ አይቻላቸውም” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)

4

ባሕር ዳር፡ የካቲት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከገቢዎች ሚኒስቴር ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር የዕውቅና እና የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ ነው።

በዕውቅና እና ንቅናቄ መድረኩ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የገቢዎች ሚኒስትር ድኤታ ዳዊት ውብሸት፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በገቢዎች ሚኒስቴር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ካሳሁን ደመመ ሀገር የያዘችውን የገቢ ዕቅድ ለማሳካት የክልሉ ወቅታዊ ችግሮችም ውስጥ ሆነን በገቢው ዘርፍ አበረታች ሥራዎችን አከናውነናል ነው ያሉት። ግብር ከፋዮች ለነበራቸው አበርክቶ ምስጋና አቅርበዋል።

ዕውቅናው አሁን ባለን መረጃ መሠረት የተወሰነ እንጅ ወደፊት በሚኖር የሥራ እንቅስቃሴ ዋስትና ሊኾን አይችልም ነው ያሉት። አሁን ባገኛችሁት እውቅና ሳትዘናጉ ሁሌም ሕግ አክባሪ መኾን ይገባችኋል ብለዋል፡፡ ሌሎች ግብር ከፋዮችም ከዚህ መነሻ ትምህርት በመውሰድ ለበለጠ ተወዳዳሪነት ልትዘጋጁ ይገባል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ሀገር፣ መንግሥት፣ ሕዝብ እና ግብር የማይነጣጠሉ የአንድ ቤት አራት ምሶሶዎች ናቸው ብለዋል። ዜጎች በነጻነት እና በኩራት ሠርተው ለመኖር ሀገር ያስፈልጋቸዋል፤ ሀገር ያለ ሕዝብ እና መንግሥት፤ መንግሥት ደግሞ ያለግብር ሊቆሙ አይቻላቸውም ነው ያሉት።

ግብር ተራ ሳንቲም የመሰብሰብ ጉዳይ አይደለም። ግብር የፍትሕ አገልግሎት የማግኘት ጉዳይ ነው፤ ግብር የመሠረተ ልማት፣ የትምህርት፣ የጤና፤ የንፁሕ መጠጥ ውኃ፣ የተመቻቸ መንገድ አቅርቦት ጉዳይ ነው፤ ግብር የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል በጸጥታ ችግር ውስጥም ኾኖ ከፍተኛ የኾነ የግብር አሰባሰብ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል። ይህ ሲባል ግን ከኢኮኖሚ ዕድገቱ፣ ከወጪ ፍላጎታችን፣ ከሌሎች ሀገሮች እና ከአጎራባች አቻ ክልሎች ጋር ሲመዘን ብዙ የሚቀረን አለ ነው ያሉት።

ግብር ከፋዩ የግብር ሕጎችን እንዲያውቅ ግንዛቤ መፍጠርን፤ የገቢውን መጠን ለማወቅ ጥናት ማድረግን፣ መረጃ ማፈላለግን፣ በገቢ ልክ ግብር መወሰን እና መሰብሰብን ይጠይቃል ነው ያሉት። የግብር አጣጣሉ ፍትሐዊ መኾኑን ማረጋገጥን እንደሚገባም ገልጸዋል።

ግብር መሰብሰብ ውስብስብ መኾኑንም ተናግረዋል።
ቢሮው በዲጅታላይዜሽን የታገዘ ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ መኾኑን ተናግረዋል። የሥነ ምግባር ጉድለት ያለባቸው ባለሙያዎቻችን ላይ አምርረን እርምጃ እየወሰድን ነው ብለዋል።

በውስጥ የዕውቀትና ክህሎት አቅም ማነስ፣ የቅንነት እና ቅልጥፍ እና መጓደል፣ የሥነ ምግባር ችግር፣ የግብዓት እጥረት፣ የግብር አጣጣል የፍትሐዊነት መጓደል የግብር አሰባሰብ ችግሮች መኾናቸውን ተናግረዋል።

በግብር ከፋዮች በኩል ደግሞ የግብር ሕግ ተገዥነት መጓደል፣ ግብርን በትክክል እና በወቅቱ አለማሳወቅ፣ አለመክፈል፣ ደረሰኝ አለመቁረጥ፣ ታክስ አልሰበሰብንም የማለት ችግር አለ ነው ያሉት።
ግብር ከፋዮች አደራቸው እጥፍ ድርብ መኾኑን ገልጸዋል።

በ2018 በጀት ዓመት 100 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው ያሉት ኀላፊው እስካሁን 50 ቢሊዮን ሰብስበን ታሪክ ሠርተናል ነው ያሉት።

ይህ እቅድ ካለን አቅም አኳያ ሲታይ ግን ያነሰ ነው፤ ክልሉ ያለበትን ነበራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የታቀደ እንጅ በቂ ነው ተብሎ አይወሰድም ብለዋል። በቀሪ ወራት ቀሪውን በጋራ ማሳካት ክልሉን ተወዳዳሪ ማድረግ መኾኑን ገልጸዋል። ለታማኝ ግብር ከፋዮችም ምስጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገራችን የቀደምት ሥልጣኔዎች እናት፣ ባርነትን ታግለው ያሸነፉ የክንደ ብርቱዎች ምድር ናት” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next article39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እየተካሄደ ነው።