“ሀገራችን የቀደምት ሥልጣኔዎች እናት፣ ባርነትን ታግለው ያሸነፉ የክንደ ብርቱዎች ምድር ናት” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

5

ባሕር ዳር፡ የካቲት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት፣ የሥልጣኔ እና የብልጽግና ንጋት አብሣሪ ኾና ቀጥላለች ነው ያሉት።

ሺህ ዘመናትን ቀድማ የሥልጣኔን ቀለም ያሠመረች፣ ጀግንነትን በተራራዎቿ ደረት ያተመች፤ ዛሬም አህጉራዊ ብልጽግናን አውጃ እየሠራች ያለች፣ የአህጉሩ ዐቅም እና ጌጥ ናት ብለዋል።

ሀገራችን የቀደምት ሥልጣኔዎች እናት፣ ባርነትን ታግለው ያሸነፉ የክንደ ብርቱዎች ምድር ናት ነው ያሉት። 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በመጪዎቹ ሁለት ቀናት በውቧ መዲናችን አዲስ አበባ ይካሄዳል ብለዋል።

በጉባዔው የሚሳተፉ የሀገራት መሪዎችና የልዑካን ቡድኖቻቸው ወደ መዲናቸው እና ወደ ሁለተኛ ቤታቸው በመግባት ላይ ናቸው። እኛ ኢትዮጵያውያንም በደመቀ እንግዳ ተቀባይነት እንኳን አርሂቡ ብለን እየተቀበልናቸው ነው ብለዋል።

በመሪዎች ጉባዔ ላይ የአህጉሪቱ በትናንት ጥረት፣ ስኬት እና በነገ ብሩህ ተስፋ ላይ ምክክር ይካሄድበታል። በተጨማሪም የአጀንዳ 2063 ትግበራን ጨምሮ በልዩ ልዩ አህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ ይመከራል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የኅብረቱ መቀመጫ ከመሆን ባለፈ ለተፈረሙ እና ለተጀመሩ አህጉራዊ አጀንዳዎች ትግበራ ስሟ በደጋጋሚ የሚነሣ የተግባር ምሳሌ ናት።

እንደ ዕንቁ እየደመቀች በምትገኘው የአፍሪካውያን መዲና አዲስ አበባ የሚካሄደው አህጉራዊ ጉባዔ የተሳካ እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበምስጢር የሚሰቃዩ እናቶችን ታሪክ የሚቀይረው የሕክምና መፍትሔ።