በምስጢር የሚሰቃዩ እናቶችን ታሪክ የሚቀይረው የሕክምና መፍትሔ።

5
ባሕር ዳር፡ የካቲት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ በርካታ እናቶች የማህጸን መውጣት ችግር አጋጥሟቸው ለረጅም ዓመታት በስውር ሕመም እንደሚሰቃዩ ይነገራል። ይሁን እንጂ ባለሙያዎች ችግሩ ቀድሞ ከተለየ በቀላሉ በሕክምና ሊድን የሚችል መኾኑን በመግለጽ እናቶች ሕመማቸውን ደብቀው መቆየት እንደማይገባቸው ይገልጻሉ።
የማህጸን መውጣት ምንድን ነው? መንስኤዎቹስ?
እንደ ማህጸን እና ጽንስ ስፔሻሊስት ዶክተር በላይነው ቀለብ ማብራሪያ፣ የማህጸን መውጣት ማለት ማህጸን እና በአካባቢው ያሉ አካላት ደጋፊ ጡንቻዎቻቸው በመላላታቸው ምክንያት ወደ ታች መንሸራተት ወይም መውረድ ማለት ነው።
ዋና ዋና አጋላጭ ምክንያቶች፦
👉በተደጋጋሚ መውለድ እና የተራዘመ የምጥ ቆይታ።
👉ከባድ ዕቃ መሸከም እና ከፍተኛ የሥራ ጫና።
👉ሥር የሰደደ ሳል እና የሆድ ድርቀት።
👉የሰውነት ክብደት መጨመር በተለይም ቦርጭ።
👉የዕድሜ መግፋት እና የሆርሞን መዛባት።
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
እናቶች የሚከተሉት ምልክቶች ሲታዩባቸው በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ይኖርባቸዋል፦
👉በብልት አካባቢ የክብደት ወይም የመጫን ስሜት መሰማት።
👉ያልተለመደ የፈሳሽ መኖር እና በግንኙነት ወቅት ሕመም መኖር።
👉ሽንትን መቆጣጠር አለመቻል ወይም የመቆርቆር ስሜት።
👉በከባድ ሁኔታ ደግሞ ከብልት ውጭ የሚታይ ወጣ ያለ ነገር መኖር።
የሕክምና አማራጮች
ሕክምናው እንደ ሕመሙ ደረጃ እና እንደ እናቶች ፍላጎት ይወሰናል፦
ችግሩ ቀለል ያለ ሲኾን የሰውነት ክብደትን መቀነስ፣ የሆድ ድርቀትን መከላከል እና የዳሌ ጡንቻዎችን የሚያጠናክሩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ይገባል።
ከባድ ደረጃ ላይ በተለይም በቀዶ ጥገና የሚሠራበት ጀረጃ ላይ ሲደርስ ደግሞ ወደፊት ልጅ መውለድ ለሚፈልጉ እናቶች ማህጸንን ወደ ቦታው የመመለስ፣ ለሌሎች ደግሞ እንደ አስፈላጊነቱ ማህጸንን ሙሉ በሙሉ የማስወገድ ሕክምና ይሰጣል።
የመከላከያ መንገዶች
የማህጸን እና ጽንስ ስፔሻሊስት ዶክተር በላይነው ቀለብ እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ፣ ከወሊድ በኋላ የሰውነት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ፣ በፋይበር የበለጸጉ ምግቦችን በመመገብ ድርቀትን እንዲከላከሉ እና ከባድ ሸክሞችን እንዲቀንሱ መክረዋል።
ችግሩ “የፈጣሪ ቁጣ ወይም እርግማን አይደለም” የሕክምና ባለሙያው እናቶች ሳይፈሩ እና ሳይደብቁ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ጤንነታቸውን እንዲመልሱም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የምርጫ ውድድራችን የሕዝባችን ሰላም እና የሀገርን አንድነት እንዳያደፈርስ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል” አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ
Next article“ሀገራችን የቀደምት ሥልጣኔዎች እናት፣ ባርነትን ታግለው ያሸነፉ የክንደ ብርቱዎች ምድር ናት” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ