“የምርጫ ውድድራችን የሕዝባችን ሰላም እና የሀገርን አንድነት እንዳያደፈርስ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል” አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ

4
ባሕር ዳር፡ የካቲት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በባሕር ዳር እየተወያየ ነው።
በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሣቢ ተስፋሁን ዓለምነህ ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገች መኾኗን ገልጸዋል።
ውይይቱ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ ያለመ መኾኑንም ተናግረዋል። “በየፊናችን ለምርጫ ውድድር እናደርጋለን፣ ውድድራችን ግን የሕዝባችን ሰላም እና የሀገርን አንድነት እንዳያደፈርስ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል” ነው ያሉት።
ምርጫ ካለ አሸናፊ እና ተሸናፊ ፓርቲ ይኖራል፤ ነገር ግን አሸናፊ ሀገር እና አሸናፊ ዴሞክራሲ መኖር አለበት፤ ለዚህ ደግሞ በጋራ መሥራት አለብን ብለዋል።
ለምርጫው የሚደረግ ውድድር እና ቅስቀሳ ሰላምን የሚያደፍርስ እንዳይኾን ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ዴሞክራሲን እናመጣለን እያልን ዴሞክራሲን እንዳናጠፋ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል ነው ያሉት።
ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ መኾኑንም ገልጸዋል። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ መድረክ እየተፈጠረ መኾኑን አንስተዋል።
መንግሥት የፖለቲካ መሕዳሩን እንዲያሳፋ፣ ለምርጫ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ የሕዝብን ሰላም እንዲጠብቅ የምንጠይቅበት መድረክ ነውም ብለዋል።
የራሳችን ሃሳብ አለን፣ ሀገር፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና የፖለቲካ ምህዳር ደግሞ የጋራችን ነው ብለዋል። ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ በጋራ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማሰብ እንደሚገባ የተናገሩት ሠብሣቢው የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ሳያስከብሩ የሚደረጉ ውድድሮች ዋጋ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ወደ ምርጫ ቅስቀሳ ስንገባ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ምን ማድረግ አለብን የሚለው ላይ መምከር አለብንም ብለዋል።
ሀገርን ታሳቢ አድርገን ከተወዳደርን አሸናፊዎች እንኾናለን ነው ያሉት። ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ሀገር የጋራ አጀንዳችን ነው ብለዋል።
መንግሥት እንደ መንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩን እንዲወጣ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ የምንመክርበት መድረክ ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ጉዳይ ማኅበረሰብን የመለወጥ ጉዳይ ነው።
Next articleበምስጢር የሚሰቃዩ እናቶችን ታሪክ የሚቀይረው የሕክምና መፍትሔ።