የምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ጉዳይ ማኅበረሰብን የመለወጥ ጉዳይ ነው።

6

ባሕር ዳር፡ የካቲት 05/2018ዓ.ም (አሚኮ) በሥርዓተ ምግብ ምክንያት የሚፈጠሩ የመቀንጨር እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን የሚፈታ የሥርዓተ ምግብ ሽግግር እና የሥነ አመጋገብ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል።

ፍኖተ ካርታውን ወደ ተግባር ለማስገባትም የሚመለከታቸው አጋር እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት ተደርጎበታል።

የርእሰ መሥተዳድሩ የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም አማካሪ ባዘዘው ጫኔ የምግብ እና ሥርዓተ ምግብ የልማት፣ የብልጽግና እና ኅብረተሰብን የመለወጥ ጉዳይ ነው ብለዋል። መንግሥት ሀገርን እና ሕዝብን ለመቀየር ከሚቀይሳቸው ፖሊሲዎች እና ስትራቴጅዎች ተነጥሎ የሚታይ አይደለም ብለዋል።

የምግብ እና ሥርዓተ ምግብ በቂ ምርት ያለማምረት፣ የሚመረተው ምግብ በቂ ንጥረ ምግብን የያዘ አለመኾኑ፣ ሕገ ወጥ ንግድ የበዛበት መኾኑ ችግሩ እንዲወሳሰብ ያደርገዋል ብለዋል። ይህንን ውስብስብ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ነውም ብለዋል።

የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታም ውጤታማ የሚኾነው ተቋማት ተቀናጅተው ሢሠሩ እንደኾነ ጠቁመዋል። ዘርፉ በርካታ ተዋናዮች የሚሳተፉበት በመኾኑ ሁሉም አካላት ተቀናጅተው መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የአማራ ክልል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሊቃውንት ይኽይስ (ዶ.ር) የሥርዓተ ምግብ ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ መኾኑን ገልጸዋል።

እንደ ሀገርም የሥርዓተ ምግብ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ነው ብለዋል። በአማራ ክልልም ስር የሰደደውን የአመጋገብ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የሥርዓተ ምግብ ሽግግር እና የሥነ አመጋገብ ፍኖተ ካርታው ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚተገበር ነው ብለዋል። ፍኖተ ካርታው በአመጋገብ ሥርዓት ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የምግብ ሥርዓት ሽግግር እና ኒውትሬሽን ቡድን ክላስተር አንድ አስተባባሪ መሠረት ጸጋየ ፍኖተ ካርታው በሰባት ክላስተሮች የተዘጋጀ ስለመኾኑ አብራርተዋል።

በበለጸገ ምግብ አቅርቦት፣ በአመጋገብ ሥርዓት፣ በሕግ ማዕቀፎች፣ በቴክኖሎጅ አቅርቦት፣ በገበያ ተደራሽነት፣ በኀይል አማራጭ አቅርቦት እና በተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዙሪያ ሰፊ ሥራዎች እንደሚሠሩም አመላክተዋል።

ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቢሲኒያ ባንክ ባልታሰበው ሲሳይ መርሐ ግብሩ ለዕድለኛው ባለሁለት መኝታ አፓርትመንት አስረከበ።