የዓድዋ ድል የቅኝ ግዛት ሰንሰለትን በመበጠስ ኢትዮጵያን የነፃነት ተምሳሌት አድርጓታል።

7

አዲስ አበባ፡ የካቲት 05/2018ዓ.ም (አሚኮ) የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ሁለተኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ “የዓድዋ ትሩፋቶች ለዛሬዋ ኢትዮጵያ እና ለነገው ትውልድ” በሚል መሪ መልዕክት የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ያለውን ፋይዳ የሚዘክሩ ሃሳቦች ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው እንደገለጹት የዓድዋ ድል የቅኝ ግዛት ሰንሰለትን በመበጠስ ኢትዮጵያን የነፃነት ተምሳሌት አድርጓታል።

ድሉ አንዱ ለሌላው የሞተበት፣ የሰውነት ክብር እና ኢትዮጵያዊነት የጸናበት መኾኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ ይህም በነፃነት ያለመደራደርን እና አልሸነፍ ባይነትን ለትውልድ ማውረሱን ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል ቱሩፋት የኢትዮጵያ ሠራዊት በተሰለፈበት ዐውደ-ውጊያ ሁሉ አሸናፊ እንዲኾን የጀግንነት መሠረት መኾኑንም አክለዋል።

የዓድዋ ሙዚየም ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ቤኮ(ዶ.ር) በበኩላቸው ዓድዋ የአፍሪካ ዕጣ ፈንታ ቅኝ ግዛት ነው የሚለውን እና የነጮችን የበላይነት እሳቤ የሻረ ድል መኾኑን ተናግረዋል።

ከዓድዋ ድል በኋላ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ መጽናቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የአጼ ምኒልክ ዝና በዓለም እንዲናኝ እና የዓድዋ ጀግኖች ለጥቁር ሕዝቦች አርዓያ እንዲኾኑ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

ዶክተር ዮሴፍ የዓድዋ ድል የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ እንዲመሠረት እና ኢትዮጵያ የአፍሪካ እምብርት ኾና እንድትቀጥል ፋና ወጊ ሚና መጫወቱንም አስረድተዋል።

በ1928 ዓ.ም የፋሺስት ወረራ ወቅትም አሜሪካውያን እና ሌሎች የነፃነት ታጋዮች ለኢትዮጵያ ያሳዩት ወገንተኝነት የዚሁ የድል ትሩፋት መኾኑን አንስተዋል።

በሙዚየሙ አዳራሽ በተካሄደው በዚህ የፓናል ውይይት ላይ ከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት መሪዎች፣ አርበኞች፣ ተማሪዎች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ታዳሚ ኾነዋል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበመደበኛ የክረምት የምርት ጊዜያት የሚያጋጥምን የምርታማነት ችግር ለመቅረፍ የበጋ መስኖ ሰብል ልማት ሚናው የጎላ ነው።
Next articleአቢሲኒያ ባንክ ባልታሰበው ሲሳይ መርሐ ግብሩ ለዕድለኛው ባለሁለት መኝታ አፓርትመንት አስረከበ።