
ደባርቅ፡ የካቲት 05/2018ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ የግብርና ጉዳዮችን በሚመለከት ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያግዝ የገበሬዎች በዓል ተከብሯል።
በምርት ዘመኑ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ3 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ገልጿል።
አቶ አስማረ ታፈረ እና አቶ ይደርሳል ይመር በዳባት ወረዳ የፍኖተሰላም ቀበሌ አርሶ አደር ናቸው። በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በማልማታቸው ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በመደበኛ የክረምት የምርት ጊዜያት የሚያጋጥምን የምርታማነት ችግር ለመቅረፍ የበጋ መስኖ ሰብል ልማት ሚናው የጎላ በመኾኑ ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
ከግብርና ተቋማት በሚቀርብላቸው የግብዓት ድጋፍ እና ባለሙያዎች በሚሰጧቸው የግብርና ምክረሃሳቦች በመመራት ውጤታማነታቸውን እያሳደጉ መኾኑንም አብራርተዋል።
የዳባት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እሸቱ ሲሳይ በወረዳው ከ280 በላይ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የሚያገኙት ጥቅም እያደገ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት በራሳቸው ተነሳሽነት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን እያለሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
አርሶ አደሮቹ ምርቱን ከብክነት ለመከላከል ከግብርና ባለሙያዎች ጋር ተቀራርበው የክትትል ሥራዎችን ማከናዎን እንደሚጠበቅባቸውም አመላክተዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የመስኖ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ቡድን መሪ ተክለ ማርያም ገብረሥላሴ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አስቻይ ሁኔታ ከሚፈጥሩ ሁኔታዎች መካከል የበጋ መስኖ ሰብል ልማት አንዱ ነው ብለዋል። ለዚህም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በዞኑ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በመደበኛ የክረምት የምርት ጊዜ ስንዴ አምርተው የማያውቁ ቆላማ አካባቢዎች ጭምር ተጠቃሚ እየኾኑ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
