
ባሕር ዳር፡ የካቲት 05/2018ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሸን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እና የአፍሪካ ጣሊያን ፎረምን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ በከተማ የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳር ልማት ከተሞችን ጽዱ እና ውብ ማድረግ ብሎም የአካባቢ ብክለትን የቀነሱ ደማቅ ከተሞች የመፍጠር ተግባር በመዲናዋ ጀምራ በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች እያስቀጠለች እንደምትገኝ ነው የተናገሩት።
ከፕላስቲክ የጸዳ አካባቢን ለመፍጠር የአንድ ጊዜ ፕላስቲክ መያዣዎችን በመከልከልም ለአካባቢ ጥበቃ ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም አስመስክራለች ብለዋል። በቀጣይነትም የውኃ ሃብቷን በአግባቡ እና ውጤታማ በኾነ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችሉ ሁለንተናዊ ርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝም ጠቅሰዋል።
በመዲናዋም ከአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ አስቀድሞ የአፍሪካ ጣሊያን ፎረም እንደምታካሂድም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት። ይህም የአፍሪካ እና የጣሊያንን ግንኙነት በአፍሪካ አህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ የትብብር ማዕቀፎች ይበልጥ እንዲጠናከር የሚያደርግ መኾኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ታላቅ የጋራ ፎረም መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከሮም ውጭ ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያው መኾኑንም ገልጸዋል። በአፍሪካ ደረጃም ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ መዳረሻ መኾኗን ነው የጠቀሱት።
ይህም ኢትዮጵያን ከሌሎች አፍሪካ ሀገሮች ጋር በማስተሳሰር ያላትን ከፍተኛ አቅም የሚያሳይ መኾኑን ተናግረዋል።
የጉባኤው ማዕከላዊ አጀንዳ እ.ኤ.አ በ2014 በአውሮፖ ሮም ይፋ የተደረገውን ልማታዊ ዕቅድ የመገምገም እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ መኾኑንም ገልጸዋል። የጉባኤው ዋና ዋና አምዶች በኾኑት በኢነርጂ፣ በግብርና፣ በትምህርትና ሥልጠና፣ በጤና፣ በውኃ አጠቃቀም እና በመሠረተ ልማት ኢትዮጵያ በርካታ ተሞክሮዎችን ማቅረብ እና አጋርነቶችን ለመመሥረት የሚያስችላት ቁመና ላይ ትገኛለች ብለዋል።
በእነዚህ ጉባኤዎች ርእሰ ብሔሮች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ 17ሺህ የልዑካን ቡድን አባላት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
እነዚህን ጉባኤዎች ለመዘገብ ከ800 በላይ የሚዲያ ባለሙያዎች ፈቃድ መጠየቃቸውንም ገልጸዋል። በቀጣይ ቀናት የአህጉሪቱ ዋና ዋና ሚዲያዎች ዐይን እና ጆሮ ኢትዮጵያ ላይ እንደሚያነጣጥር ነው የጠቀሱት።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሚያስጠብቅ እና ከግብ በሚያደርሱ ውይይቶች ላይ ለመሳተፍ መዘጋጀቷን ነው ያነሱት። በዚህም የአፍሪካ የጋራ ጥቅሞችን ለማረጋገጥ የበኩሏን ጥረት ታደርጋለች ነው ያሉት።
የአፍሪካ መሪዎች እና ልዑካን በቆይታቸው ከዲፕሎማሲ ሥራዎቻቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያን የልማት ሥራዎች እና የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲጎበኙ እና በቀጣይነት እየተመዘገቡ ያሉ የልማት ውጤቶችን እንዲመለከቱ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
እንደ አስተናጋጅ ሀገር ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ መሪዎች፣ ልዑክ እና እንግዶች ተቀብላ ከማስተናገድ ባሻገር በርካታ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ለማድረግ ዝግጁ መኾኗን ተናግረዋል።
የኅብረቱ መቀመጫ እና የአፍሪካ ማዕከላዊ የኾነችው አዲስ አበባ እንግዶችን ተቀብላ ለማስተናገድ የተሟላ ዝግጅት ማድረጓንም ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
