
ደብረ ብርሃን: የካቲት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን “አርቆ ማየት፣ አልቆ መሥራት” በሚል መሪ መልዕክት የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎች የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን በደብረ ብርሃን ከተማ እየገመገመ ነው።
ዞኑ ያለበትን የጸጥታ ችግር በመቋቋም በኢንቨስትመንት እና በመምሪያዎች አፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ውጤት እንደተመዘገበ በግምገማው ተነስቷል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በተከናወኑ የተቀናጁ ሥራዎች ተጨባጭ የሰላም ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል። ውጤታማ የቀውስ ጊዜ አመራር በመስጠት እና የሕዝብን ተሳትፎ በማሳደግ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራት ስኬታማ እንዲኾኑ መደረጉንም ገልጸዋል።
በተለይም በኢንቨስትመንት ዘርፍ 34 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 255 ባለሀብቶችን መሳብ መቻሉን ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል። በግብርናው ዘርፍም አርሶ አደሮችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ አበረታች ውጤት መገኘቱን አመላክተዋል።
በማዕድን፣ በጤና እና በትምህርት ዘርፎችም ሕዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት መከናወናቸውም ተነስቷል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤልያስ አበበ ባለፉት ስድስት ወራት 13 የዞን መምሪያዎች በክልል ደረጃ በአፈጻጸማቸው አንደኛ መውጣታቸውን ገልጸዋል።
ይህም ዞኑ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥም የማይበገር የመሪነት ሥርዓት መገንባቱ ማሳያ ነው ብለዋል። ኾኖም አሁንም የሰላም እጦት እና የዜጎች መፈናቀል መኖሩን የጠቀሱት ኀላፊው ሰላምን የማጽናት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ሰዓዳ ኢብራሒም በቀጣይ ጽንፈኝነትን መታገል፣ መዋቅርን ማጠናከር እና ግጭትን ተከትሎ የሚፈጸሙ ዝርፊያዎችን መከላከል በትኩረት እንደሚሠራበት አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
