
ባሕር ዳር: የካቲት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ኅብረት ቲክቶክ ተጠቃሚዎችን በተለይም ሕጻናትን እና ወጣቶችን ለሱስ በሚያጋልጡ የንድፍ ባህሪያቱ ላይ ማሻሻያ እንዲያደርግ አሳስቧል።
ከሰሞኑ አልጀዚራ ጉዳዩን ሲዘግብ መተግበሪያው የሚጠቀምባቸው ማለቂያ የሌለው ስክሮል ቪዲዮዎችን በራሱ ጊዜ ማስጀመር እና ተደጋጋሚ የማሳሰቢያ መልዕክቶች ተጠቃሚዎች ሳያስቡት ለረጅም ሰዓት በመተግበሪያው ላይ እንዲቆዩ በማድረግ የአውሮፓን የዲጂታል አገልግሎቶች ሕግ (DSA) ጥሷል ብሏል።
በተለይም ከ12 እስከ 15 ዓመት የኾኑ 7 በመቶ ያህሉ ሕጻናት በቀን ከ4 እስከ 5 ሰዓታት መተግበሪያው ላይ እንደሚያሳልፉ የተገኘው መረጃ በአዕምሮ ጤና እና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ አደጋ እንደሚጋርጥ ኅብረቱ ገልጿል።
ጤና እና ቴክኖሎጂን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርገው ሄልዝቴክዲጂታል የተባለ ድረ ገጽ በበኩሉ ቲክቶክን ሱስ አስያዥ የሚያደርጉት ዋና ምክንያቶች የተጠቃሚውን ፍላጎት አጥንቶ የሚቀርበው ስልተ ቀመር (አልጎሪዝም) እና አሰልቺ ያልኾኑት አጫጭር ቪዲዮዎች መኾናቸውን ይተነትናል።
ይህም ተጠቃሚዎች ከመተግበሪያው ጋር ጥልቅ ስሜታዊ ትስስር እንዲፈጥሩ እና ለረጅም ሰዓት እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል። ቲክቶክ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለኾኑ ተጠቃሚዎች የ60 ደቂቃ የጊዜ ገደብ ቢጥልም ተጠቃሚው የይለፍ ቃል በማስገባት ተጨማሪ ጊዜ መጠቀም መቻሉ የቁጥጥሩን ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል።
የቲክቶክ አጠቃቀም ወደ ሱስ መለወጡን ከሚያሳዩ ምልክቶች መካከል ለ’ላይክ’ ከመጠን በላይ መጨነቅ፣ የዕለት ተዕለት ሥራን እና ትምህርትን ችላ ማለት፣ እንደ እንቅልፍ እጦት እና ራስ ምታት ያሉ የጤና ችግሮች ይጠቀሳሉ።
ድረ ገጹ ችግሩን ለመከላከልም ተጠቃሚዎች ለተወሰነ ጊዜ ከዲጂታል መሣሪያዎች በመራቅ (Digital Detox) ለሕይወት ቅድሚያ ለሚሰጧቸው ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጡ መክሯል። ችግሩ ከአቅም በላይ ከኾነ ደግሞ የባለሙያ ምክር ማግኘት አስፈላጊ መኾኑ ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
