
ባሕር ዳር፡ የካቲት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በወንጀል ተከስሰው ጥፋተኛ የተባሉ ዜጎች፣ ቅጣታቸውን ከፈጸሙ በኋላ የቀድሞው የወንጀል ታሪካቸው በቀጣይ ሕይወታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር “መሰየም” በሚባል ሕጋዊ ሂደት ስማቸውን ማጽዳት እንደሚችሉ ሕጉ ያስቀምጣል።
ለመኾኑ መሰየም ምንድን ነው?
በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የመደበኛ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቢ-ሕግ አማረ ሽቴ ለአሚኮ እንደገለጹት መሰየም ማለት ቅጣቱን የጨረሰ፣ በይርጋ ወይም በይቅርታ የቀረለት ወይም በአመክሮ የተለቀቀ ማንኛውም ሰው ከመቀጣቱ በፊት የነበረው ንጹሕ ስም እንዲመለስለት እና ፍርዱ ከሪከርድ እንዲሰረዝለት የሚጠይቅበት የሕግ ሂደት ነው።
ይህ መብት በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 232 ላይ ተደንግጎ ይገኛል።
ዐቃቢ ሕጉ አክለውም መሰየም እንደ መብት በይገባኛል የሚጠየቅ ሳይኾን “በመልካም ሥራ” የሚገኝ መኾኑን እና አቤቱታውም ውሳኔ ለሰጠው ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት አስረድተዋል።
ለመሰየም የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ምን ይኾኑ?
አንድ ፍርደኛ ስሙ እንዲታደስለት የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት ይኖርበታል፦
👉የጽኑ እስራት ቅጣት ከኾነ ቅጣቱ ከተፈጸመበት ወይም በይቅርታ ከተለቀቀበት ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ አምስት ዓመት ማለፍ አለበት። በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ ቢያንስ ሁለት ዓመት መቆየት ይጠበቅበታል።
👉በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ ምንም ዓይነት በእስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ሳይፈጽም በመልካም ጠባይ መኖር ይኖርበታል።
👉በፍርድ የተወሰነበትን ካሳ እና ማንኛውንም የዳኝነት ኪሳራ በሚገባ ከፍሎ መጨረስ አለበት።
👉በሕዝባዊ ወይም ማኅበራዊ አገልግሎት መስክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከተ፣ ሕጉ ካስቀመጠው የጊዜ ገደብ በፊት መሰየም ሊፈቀድለት እንደሚችል በአንቀጽ 234 ተደንግጓል።
👉የመሰየም ውጤት እና ውሳኔውን የመሻር ሁኔታ ይኖር ይኾን?
አንድ ሰው የመሰየም ውሳኔ ካገኘ በኋላ የሚያገኛቸው መብቶች በአንቀጽ 235 ተቀምጠዋል።
ከእነዚህም መካከል የቅጣት ፍርዱ ከወንጀለኞች መዝገብ የማስፋቅ መብትን እንደሚያገኝ ተገልጿል።
ግለሰቡ እንዳልተፈረደበት ተቆጥሮ በሙያው የመሥራት እና ሕዝባዊ መብቶቹን የመጠቀም ችሎታው እንዲመለስለት እንደሚደረግም ተጠቁሟል።
የተሰረዘውን ቅጣት አንስቶ ተቀጭውን መውቀስ “በስም ማጥፋት” ወንጀል ሊያስቀጣ እንደሚችልም ነው ሕጉ ያስቀመጠው።
ኾኖም አንድ ሰው ከተሰየመ በኋላ ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ በጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ከባድ ወንጀል ከፈጸመ የተሰጠው የመሰየም ውሳኔ እንደሚሰረዝ በአንቀጽ 237 ተደንግጓል።
የሰየመው ፍርድ ቤት ጥያቄውን ውድቅ ካደረገውም ግለሰቡ በድጋሚ ጥያቄ ለማቅረብ ሁለት ዓመት መጠበቅ ይኖርበታል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለኝ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
