ፋይዳ አካታች የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ነው።

20
ባሕር ዳር: የካቲት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በኢትዮጵያ ውስጥ ግለሰቦች ማንነታቸው በዘመናዊ መንገድ እንዲረጋገጥ የሚያስችል ብሔራዊ መለያ ነው። የመንግሥት እና የግል አገልግሎቶችን ዘመናዊ፣ አስተማማኝ እና ፈጣን በኾነ መንገድ ለመስጠትም ኾነ ለማግኘት የሚያስችል የዲጂታል ሥርዓት ነው።

የአንድን ግለሰብ መረጃ በአንድ ማዕከል ስለሚያቀናጅ መረጃን ደጋግሞ ከመስጠት ይታደጋል። አንድ ሰው አንድ መታወቂያ ብቻ እንዲኖረው የሚያስችል ነው። ይህም ስርቆትን እና ማጭበርበርን በመከላከል ለዜጎች እና ለተቋማት አስተማማኝ ደኅንነት
ይፈጥራል። በዲጂታል የታገዘ በመኾኑም በአካል መገኘት ሳያስፈልግ በርካታ ሥራዎችን በድረ-ገጽ ወይም በስልክ ለማከናወን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በዚህም ጊዜን እና የሀብት ብክነትን ይቀንሳል።
በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላት ዳይሬክተር ሳሚናስ በላይነህ ፋይዳ ዘመናዊ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መኾኑን ይገልጻሉ። ፋይዳ በአገልግሎት ሰጭዎች እና አገልግሎት ፈላጊዎች መካከል እምነትን የሚፈጥር የመተማመኛ ማዕቀፍ ነው ብለዋል። ተቋማት በዲጂታል የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት የተቀላጠፈ አገልግሎትን ለመስጠት ዲጂታል መታወቂያ ሁነኛ መሣሪያ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ፋይዳ በቀላሉ የሚገኝ ውጣ ውረድ አልባ አካታች የመታወቂያ ሥርዓት ስለመኾኑም አቶ ሳሚናስ አንስተዋል። የፋይዳ ምዝገባው በነጻ ይከናወናል። ማንኛውም ዜጋ ማንነትን የሚገልጽ ማስረጃ ይዞ በመቅረብ መመዝገብ እና አሻራ በመሥጠት የዲጂታል መታወቂያውን ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል።
ለምዝገባው በመላው ኢትዮጵያ ከ7 ሺህ በላይ የመመዝገቢያ ማሽኖችም ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት። አቶ ሳሚናስ እንዳብራሩት የፋይዳ መታወቂያ ቀላል እና ለአጠቃቀም ምቹ የኾኑ የአያያዝ አማራጮችንም የዘረጋ ነው። በስልክ ቁጥር የሚላከውን አጭር የጽሑፍ መልዕክት፣ በስማርት ስልክ እና በታተመ ካርድ የመጠቀም አማራጮችንም ያካተተ ነው። ሁሉም አማራጮች በሕግ ፊት እኩል ተቀባይነት እንዳላቸውም አብራርተዋል። አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ሁሉንም አማራጮች በእኩል ተቀብለው ደንበኞቻቸውን እንዲያስተናግዱም አሳስበዋል።

ነገር ግን በካርድ ኅትመት አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጠው ከኢትዮ ቴሌኮም እና ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ጋር ለተደረጉ ስምምነቶች ብቻ በመኾኑ ዜጎች ከሌሎች አካላት በሚታተሙ ካርዶች ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
አሁን ላይ የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ በዘመቻ መልክ እየተካሄደ መኾኑን ገልጸው ሁሉም ዜጋ በወቅቱ በመመዝገብ መታወቂያውን መያዝ እንደሚገባ አስረድተዋል። መታወቂያውን ያወጡ ዜጎችም በወቅቱ ከባንክ ቁጥሮቻቸው ጋር ማስተሳሰር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ከግለሰብ ጀምሮ ለተቋማት እና በሀገር ደረጃ ደኅንነቱ የተረጋገጠ የመረጃ ሥርዓትን ለመገንባት ወሳኝ ስለመኾኑም አንስተዋል።

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየተለያዩ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በ48ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አሥፈጻሚ ምክር ቤት ለመሳተፍ አዲስ አበባ እየገቡ ነው።
Next articleየኢቢኤስ ቴሌቭዥን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አማን ፍስሃጽዮን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።