በሰው የመነገድ ወንጀል እና ተጠያቂነቱ።

3
ባሕር ዳር: የካቲት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎በሰው የመነገድ ወንጀል የሚባለው በአዋጅ ቁጥር 1178/2012 ላይ እንደተደነገገው ሰውን በባርነት፣ በእዳ መያዣነት፣ ለወሲብ ብዝበዛ፣ ለልመና፣ ለወንጀል ተግባር፣ ለግዳጅ ጋብቻ፣ ለማህፀን ኪራይ፣ እና መሰል ተግባራት መፈፀምን የሚያጠቃልል ነው። ወንጀሉ ሕፃናትን ለብዝበዛ ዓላማ መመልመልን፣ ማጓጓዝን፣ ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍን፣ ማስጠለልን፣ መደበቅን የሚያካትት የወንጀል ድርጊት ነው፡፡
በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የመደበኛ ወንጀሎች ዳይሬክተር ዐቃቢ ሕግ ቸኮለች እጅጉ እንዳብራሩት በሰው የመነገድ ወንጀል ድርጊት የሚፈጸመው በኀይል በማስገደድ፣ በመጥለፍ፣ በማታለል እና ሌሎችንም መንገዶች በመጠቀም ነው።
በሰዎች የመነገድ ወንጀል ከ7 ዓመት እስከ 15 ዓመት እስራት የሚደርስ ቅጣት እንደሚያስከትል አብራርተዋል። እንደ ድርጊቱ አፈጻጸም ቅጣቱ እስከ ሞት ድረስ ሊያስቀጣ እንደሚችል በአዋጁ መደንገጉን ያነሳሉ።
በሰዎች የመነገድ ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ ለተለያዩ ቅጣቶች እንደሚያጋልጥ በአዋጁ ተደንግጎ ይገኛል።
👉 ማንኛውም በሰዎች የመነገድ ወንጀልን የፈጸመ ሰው ከ7 ዓመት እስከ 15 ዓመት ፅኑ እስራት እና ከብር 20 ሺህ እስከ ብር 100 ሺህ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል።
👉 በሰው የመነገድ ሂደት ውስጥ በሚያልፈው ሰው ላይ ብዝበዛ የተፈፀመ ከኾነ ብዝበዛውን የፈፀመውም ኾነ በሂደቱ የተሳተፈ ሰው ከ7 ዓመት እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከብር 40 ሺህ እስከ 100 ሺህ በሚደርስ መቀጮ ያስቀጣል፡፡
👉 ወንጀሉ የተፈፀመው በሕጻናት፣ በአካል ጉዳተኞች፣ በአዕምሮ ሕሙማን ላይ ከኾነ፤ አደንዛዥ እፅ፣ መድኃኒት ወይም የጦር መሳሪያ በመጠቀም ከኾነ፤ ወንጀሉ በመንግሥት ሠራተኛ ወይም ባለሥልጣን የተሰጠውን ኀላፊነት መከታ በማድረግ የፈፀመው ከኾነ፤ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ፈቃድን በመጠቀም የተፈፀመ ከኾነ ቅጣቱ ከ10 ዓመት እስከ 20 ዓመት ፅኑ እስራት እና ከብር 30 ሺህ እስከ ብር 100 ሺህ በሚደርስ መቀጮ ያስቀጣል፡፡
👉 ወንጀሉ የተደራጁ የወንጀል ቡድን አባላትን በመምራት እና በማስተባበር ከተፈፀመ፣ በተጎጂው ላይ የማይድን በሽታ ካስከተለ፣ በተጎጂው ሕይወት እና ደኅንነት ላይ አደጋ ከጣለ ወይም ከባድ የአካል ጉዳት ካስከተለ ከ15 ዓመት እስከ 25 ዓመት ፅኑ እስራት እና ከብር 50 ሺህ እስከ ብር 150 ሺህ በሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡
👉 ወንጀሉ በተጎጂው ላይ ሞትን አስከትሎ ከኾነ እንደ ሁኔታው ከ15 ዓመት እስከ 25 ዓመት ወይም የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት አለያም በሞት እና አስከ ብር 200 ሺህ የገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል፡፡
👉 ለወንጀሉ መፈፀም ምቹ ሁኔታን የፈጠረ፣ ንብረቱን ለወንጀሉ መፈፀሚያነት እንዲውል መፍቀድ፣ ማከራየት፣ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከ3 ዓመት እስከ 7ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና እስከ ብር 50 ሺህ የገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል፡፡
👉 በወንጀሉ የአፈጻጸም ሂደት የተጭበረበር፣ ሀሰተኛ ወይም ሕገ ወጥ መታወቂያ ወይም የጉዞ ሰነድ ማዘጋጀት፣ መስጠት፣ ማቅረብ ወይም ይዞ መገኘት ከ5 ዓመት እስከ 15 ዓመት ፅኑ እስራት እና ከብር 10 ሺህ እስከ ብር 50 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ የሚያስቀጣ መኾኑ በአዋጁ ተደንግጓል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ በስድስት ወራት ብቻ ለ48 ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል።
Next articleበዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር 142 ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።