
ደብረ ማርቆስ: የካቲት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት እቅድ የስድስት ወርራት አፈፃፀሙን ገምግሟል። የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ የግምገማ መድረኩ ተቋማትን ከእቅድ ጀምሮ እስከ አፈፃፀም በመከታተል የሥራ ኀላፊዎች በገቡት የቃል ኪዳን ሰነድ እና በአስቀመጡት ራዕይ እና ግብ መሠረት አፈፃፀማቸውን በመመዘን የተጠያቂነት አሠራርን ለመዘርጋት ያለመ መኾኑን ገልጸዋል።
አላማችን በበጀት ዓመቱ ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን በርካታ ፀጋዎችን በማልማት እና የታቀዱ የትኩረት መስኮችን በቁርጠኝነት በመፈፀም ሥራን ወደ ፊት በማስኬድ እና በውጤቱ ትውልድን ማሻገር ነው ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ ከተማና መሠረተ ልማት መመሪያ ኀላፊ አስምሮም ሞስነህ ከዚህ በፊት የተጀመሩ ሥራዎችን ስንቅ በማድረግ እና የማኅበረሰብ ተሳትፎን በማሳደግ የበጀት ዓመቱን ውጤታማ የማድረግ ቁመና ላይ እንገኛለን ብለዋል። የተቀናጀ መሰረተ ልማት በማሟላት እና ከተማውን ፅዱ እና ምቹ ለማድረግ የታቀዱ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ተመስገን ተድላ የተቋሙን እቅድ ከፈፃሚ አካላት ጋር የጋራ አድርጎ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል። በግማሽ በጀት ዓመቱ ብቻ ለ48 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመስጠት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል። ለ1 ሺህ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ እድል መመቻቸቱንም ጠቁመዋል። በቀጣይም የፋይናንስ እና የመሠረተ ልማት ችግሮችን በጥምረት በመፍታት እና የፋብሪካ ባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እንሠራለን ብለዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ፕላንና ልማት መምሪያ ኀላፊ ማማሩ ገድፍ ባለፉት ስድስት ወራት በአብዛኛው ተቋማት የታዩ አበረታች ለውጦች በቀጣይ አምስት ዓመታት ለማሳካት የተቀመጠውን አሻጋሪ የእድገትና ዘላቂ ልማት እቅድ ለማሳካት መልካም ጅማሮ ላይ እንደሚገኙ አመላካች ናቸው ብለዋል።
በቀጣይ የተቋማትን የበጀት እና የአቅም ክፍተቶች ለይቶ በማገዝ ሁሉም የተቀራረበ አፈፃፀም እንዲያስመዝግቡ መሥራት ወሳኝ መኾኑን ጠቁመዋል።
በከተማው “የትውልድ ቁጭትን ለትውልድ ልዕልና የማነፅ ትልም” በሚል መልዕክት በተካሔደው የስድስት ወር አሻጋሪ የእድገት እና የዘላቂ ልማት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ በቀጣይ ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት መግባባት ላይ ተደርሷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
