“ቤተ መጻሕፍቱ ትውልድን የሚገነባ ዘመን አይሽሬ ቅርስ ነው” የሰቆጣ ነዋሪዎች

12
ሰቆጣ: የካቲት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በመከላከያ ሠራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አባላት ከ71 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ በሰቆጣ ከተማ ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።
ይህንን በማስመልከት አስተያየታቸውን ለአሚኮ የገለጹት የሰቆጣ ከተማ ነዋሪው በጽሐ ገብራት “የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አባላት የገነቡት ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት ለዘመናት የሚኖር የዕውቀት ቅርስ ነው “ብለዋል።
ሠራዊቱ የሀገሪቷን ሰላም ከመጠበቅ ባሻገር በመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ የሚያበረክቱት አሥተዋጽኦ በቃላት እንደማይገለጽ የገለጹት ደግሞ ኪሮሱ ገብረ መስቀል ናቸው። ይኸውም የዋግ ኽምራ ተማሪዎች ከመላው የኢትዮጵያ ተማሪ ጋር እኩል እንዲወዳደሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ዋግ ላይ አዳሪ ትምህርት ቤት እየተገነባ ባለበት በዚህ ወቅት ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ በትምህርት ዘርፉ ትልቅ ድል መኾኑን ደግሞ አማረ አካላት ነግረውናል።
የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አባላት የሠሩት ልማት ከዘመን እስከ ዘመን የሚነገር፤ ለሌሎች አርዓያ የኾነ ልማት ነው ብለዋል አቶ አማረ። ሥለተደረገው ድጋፍም ነዋሪዎቹ ከልብ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ኾነው በትብብር እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌትናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ ለጀግና መታሰቢያው ሐውልት ቢኾንም ዕዙ ግን መታሰቢያው ትውልድን የሚቀርጽ ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት እንዲኾን ወስነን ተግብረነዋል ብለዋል።
ሃብቱን ጠብቆ በማቆየት ከልጅ ወደ ልጅ የሚተላለፍ የዕውቀት ምንጭ፤ የምርምር ማጣቀሻ እና የአዋቂዎች መነሻ እንዲኾን ማድረግ እንደሚገባም ጄኔራሉ አሳስበዋል።
ዘጋቢ ፦ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየባለጸጋው በላይነህ ክንዴ አሻራ በሎጎ ሐይቅ ሪዞርት።
Next article“ጎንደር ከተማ የልማት ተጠቃሚ እንድትኾን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉ እናመሰግናለን” ወጣቶች