
አዲስ አበባ: የካቲት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ”ገበታ ለትውልድ” መርሐ-ግብር ከተገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ የኾነው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
ሪዞርቱን የገነባው የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ባለቤት ባለጸጋው በላይነህ ክንዴ ባለሃብቶች ለልማት ሲሰማሩ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ታሳቢ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ የሎጎ ሐይቅን ተንተርሶ በ13 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ሪዞርት በበላይነህ ክንዴ ጠቅላላ ተቋራጭነት እና በኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አማካሪነት የተገነባ ነው።
ፕሮጀክቱ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም ተጀምሮ ጥር 30/ 2018 ዓ.ም ለአገልግሎት የበቃ ሲኾን “የሚሠሩ እጆች እና የሚመሩ አዕምሮዎች” ተሰላስለው ጥበብን የሸመኑበት መኾኑ ተገልጿል።
የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ባለቤት እና የቦርድ ሠብሣቢ በላይነህ ክንዴ ለአሚኮ እንደገለጹት ባለሃብቶች በአንድ አካባቢ ሲሰማሩ ከንግድ ሥራ ባለፈ ማኅበራዊ ኀላፊነትንም መወጣት አለባቸው ይላሉ።
ባለጸጋው ከሪዞርቱ ግንባታ ጎን ለጎን ለአካባቢው ማኅበረሰብ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገንብተው ማስረከባቸውን አስታውቀዋል።
መንግሥት ለግል ዘርፉ የፈጠረው አመቺ የልማት ሁኔታ ለእንዲህ ያሉ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መሳካት ቁልፍ ሚና መጫወቱንም ተናግረዋል።
አማራ ክልል የቱባ ባሕል እና የበርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች መገኛ ቢኾንም በመሠረተ ልማት እጥረት ሳይገለጡ መቆየታቸውን ባለጸጋው በላይነህ ክንዴ ጠቅሰዋል።
ይህ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ግንባታ የክልሉን እና የሀገሪቱን የቱሪዝም አቅም ማሳደግ፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ በመሠረተ ልማት እጥረት ተሸፍነው የቆዩ ፀጋዎችን ማውጣት ላይ ፋይዳው የጎላ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ምርቃት የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ትብብር ምን ያህል ውጤታማ ሊኾን እንደሚችል ማሳያ መኾኑም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
