‎እጥረትን በተግባር የቀረፈው ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ

8
ባሕር ዳር: የካቲት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎ሲሚንቶ ዋነኛው የኮንስትራክሽን ግብዓት ሲኾን ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደ ሀገር ከፍተኛ እጥረት የሚከሰትበት ምርት ነበር፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ እንደ ለሚ ያሉ ግዙፍ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ በመግባታቸው ችግሩ ሲቀንስ ተስተውሏል፡፡
ለመኾኑ እንደዚህ ዓይነት ኢንዱስትሪዎች መስፋፋታቸው ለሀገር ያለው አበርክቶ ምንድን ነው?
‎የዓባይ ኮንስትራክሽን ሥራ አሥኪያጅ ዳዊት ድረስ የሲሚንቶ እጥረት ከአንድ ዓመት በፊት የኮንስትራክሽን ዘርፉን ፈትኖት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ሥራ መግባቱ በግንባታ ዘርፉ ላይ የነበረውን የሲሚንቶ እጥረት እና የዋጋ ንረት ችግር እንደፈታው ነው የጠቀሱት፡፡
‎በነበረው ችግር የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ እስከ 2 ሺህ 500 ብር ደርሶ የነበረ ሲኾን በምርት እጥረት ምክንያት ፕሮጀክቶች ይጓተቱ እና ለተጨማሪ ወጭ ይዳረጉ እንደነበር ነው የነገሩን።
‎የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከጀመረ በኋላ ሲሚንቶን በሚፈለገው መጠን እና ጊዜ ማግኘት ተችሏል፤ ዋጋውም በኩንታል 1 ሺህ 150 ብር መድረሱን ጠቁመዋል፡፡
‎የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ መምህር አርዓያ ገብረዮሐንስ ፋብሪካው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በ187 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ግዙፍ ፋብሪካ ነው ብለዋል፡፡ በ600 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው እና በመስከረም 2017 ዓ.ም ወደ ሥራ የገባው ፋብሪካው የሀገሪቱን የሲሚንቶ ገበያ በመቀየር ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት።
‎ፋብሪካው በቀን 150 ሺህ ኩንታል ስሚንቶ የማምረት አቅም ያለው ሲኾን እስካሁን 40 ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ ለገበያ አቅርቧል ብለዋል። የሀገሪቱን የሲሚንቶ ፍላጎት 50 በመቶ በመሸፈን የሲሚንቶ ዋጋ በ60 በመቶ እንዲቀንስ አድርጓል ነው ያሉት።
‎በነበረው የሲሚንቶ እጥረት ምክንያት በነጋዴዎች ሲሚንቶ ይከማችበት የነበረውን ገንዘብ በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲዘዋወር ዕድል ፈጥሯልም ብለዋል፡፡ ፋብሪካው አሁን የሚመረቱትን ኦፒሲ እና ፒፒሲ ሲሚንቶን ጨምሮ በትዕዛዝ የሚመረቱ የተለያዩ የሲሚንቶ ዓይነቶችን የማምረት አቅም ስላለው እንደ ሀገር አስተማማኝ የሲሚንቶ አቅርቦት እንዲኖር አስችሏልም ብለዋል፡፡
‎ፋብሪካው የተቋቋመባቸው ዓላማዎች የሲሚንቶ እጥረትን መቅረፍ፣ የተሻለ ቴክኖሎጅ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ባለሙያዎችን ማሠልጠን እና ገበያን ማረጋጋት ናቸው ብለዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የሲሚንቶ እጥረቱን እና የዋጋ መረጋጋቱ በሁሉም ክልሎች ተደራሽ በመኾን ተፈትቷል ብለዋል፡፡
‎ፋብሪካው የአካባቢ ብክለትን የሚከላከል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም ሲኾን በቀጣይም የማስፋፊያ ቦታ በመረከብ ወደ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ፋብሪካው ‎ከ1 ሺህ 100 በላይ ለሚኾኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲኾን ከ2 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት፡፡ ለፋብሪካው ግንባታ ከመሬታቸው ለተነሱ አርሶ አደሮች የጥሬ ዕቃ አቅራቢ ኾነው እየሠሩ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በለሚ ከተማ ሆስፒታል የመገንባት፣ የውኃ እና የኤሌክትሪክ አቅርቦት የማሟላት ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። አሁን ላይ ፋብሪካው ከእጥረት አልፎ ምርት እያለ የገበያ እጥረት መኖሩን ነው የጠቆሙልን።
‎የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ሳይንስ ትምህት ክፍል መምህርት ትዕግስት ዘላለም (ዶ.ር) የምርት እጥረት ያለባቸውን ምርቶች መሠረት ያደረጉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መገንባት ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡
ምርትን በስፋት የሚያመርቱ አቅም ያላቸው ኢንዱስትሪዎች መከፈት ቁጥሩ በየጊዜው የሚጨምር ሕዝብ ላላት እና የምርት ፍላጎት በፍጥነት እያደገ ለሚሄድ ሀገር አዋጭ ነው ይላሉ፡፡
‎እንደ ለሚ ሲሚንቶ ያሉ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸውን ፋይዳ በአራት መልኩ ሊታይ ይችላል ብለዋል፡፡ እነዚህም፡-
የቴክኖሎጂ ሽግግር፤‎ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ፤ የውጭ ምንዛሬን ማዳን እና የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚሉት ዋና ዋና በረከቶችን ይዞ እንደሚመጣ ገልጸውልናል።
‎እንደነዚህ ዓይነት ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ በመንግሥት በኩል የመሠረተ ልማት አቅርቦትን ማስፋፋት፣ ትልልቅ ድርጅቶች በአክሲዮን መልክ እንዲደራጁ ማበረታታት እና ምቹ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
‎ባለሃብቶችም የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ለአጭር ጊዜ ትርፍ ከሚሮጡባቸው ዘርፎች ወጥተው ለሀገር ዘላቂ ጠቀሜታ ባላቸው ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች ላይ መሳተፍ እንዳለባቸውም መክረዋል።
የምርት እጥረትን በዘላቂነት ለመፍታት መሰል ግዙፍ ፋብሪካዎችን ማስፋፋት እና ማበረታታት ወሳኝ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይዎት አዘዘው
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከ170 ሚሊየን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተገነቡ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጄክቶች ተጠናቅቀው ተመረቁ።
Next articleየባለጸጋው በላይነህ ክንዴ አሻራ በሎጎ ሐይቅ ሪዞርት።