
ደሴ: የካቲት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ከ170 ሚሊየን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተገነቡ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ተመርቀዋል።
በመርቃ መርሐ ግብሩ ላይ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)ን ጨምሮ ሌሎች የክልል እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ዛሬ የተመረቁት በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ እና በሐርቡ ከተማ አሥተዳደር የተገነቡ ሁለት ፕሮጀክቶች ናቸው።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ በቃሉ ወረዳ የአዳሜ፣ ገርባ እና ደጋን ከተማ እንዲሁም የሐርቡ ከተማ እና የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ከዚህ በፊት በንጹህ መጠጥ ውኃ እጥረት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል። ለውኃ ወለድ በሽታዎች ይጋለጡ እንደነበርም ተናግረዋል።
ሴቶች እና ሕጻናት ለከፋ እንግልት ይዳረጉ ነበር ያሉት ነዋሪዎቹ አሁን ላይ የንጹህ መጠጥ ውኃ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን በ2018 በጀት ዓመት ከ500 በላይ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጄክቶችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሠራ ነው። በዞኑ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ለማስፋት በሁለት መንገድ እየተሠራ መኾኑን የዞኑ ውኃ እና ኢነርጂ መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው ጽጌ ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት በተሠሩ ግንባታዎች ብቻ የዞኑን የውኃ ሽፋን ከነበረበት 70 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 71 ነጥብ 15 በመቶ አድጓል ብለዋል።
በቃሉ ወረዳ ገርባ፣ አዳሜ እና ደጋን ከተሞች፣ በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ እና በሀርቡ ከተማ ተገንብተው ለምረቃ ለበቁት አምስት የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጄክቶች ከ381 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገባቸውም አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።
አምስቱ ፕሮጄክቶች ከ140 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ።
በቀሪ ወራትም በርብርብ በመሥራት ዕቅዱን ለማሳካት ይሠራል ብለዋል።
የዞኑን ሕዝብ ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ መኾኑን ያነሱት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን በዞኑ ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ለልማት ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋንን ለማሳደግ በክልሉ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ኢንጂነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ.ር) በገጠር ከ2 ሺህ በላይ አነስተኛ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን፣ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ከ80 በላይ መካከለኛ እና ከፍተኛ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ታቅዶ ሢሠራ መቆየቱን አንስተዋል። ባለፋት ስድስት ወራትም 236 አነስተኛ የመጠጥ ውኃ ፕሮጄክቶች የተጠናቀቁ ሲኾን 16 መካከለኛ እና ከፍተኛ ፕሮጄክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል።
በተሠሩ ሥራዎች የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋንን በገጠር በ0 ነጥብ 3 በመቶ በከተማ ደግሞ በ1 ነጥብ 4 በመቶ ማሳደግ መቻሉን እና የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋን በ0 ነጥብ 5 በመቶ መጨመር እንደተቻለም ዶክተር ኢንጂነር ዳኝነት ፈንታ አንስተዋል።
በክልሉ ተገንብተው ከተጠናቀቁ 16 ከፍተኛ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች መካከል አምስቱ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ፣ አርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ እና በሐርቡ ከተማ አሥተዳደር የተገነቡ ናቸውም ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን በ25 ዓመቱ የዕድገት እና አሻጋሪ ዕቅድ በማካተት በልዩ ትኩረት እየሠራ ነው ያሉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ናቸው ። ምክትል ርእሰ መሥረዳድሩ በክልሉ ዝናብ አጠር በኾኑ አካባቢዎች ፕሮጄክቶችን በመገንባት በታዳሽ ኃይል አቅርቦት በማገዝ የውኃ ስርጭቱ ሳይቆራረጥ እንዲደርስ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
የውኃ አቅርቦቱን ከመስኖ ልማት ሥራ ጋር አቀናጅቶ በማከናወን የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርትን ለመጨመር እየተሠራ ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሊ ይመር
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
