መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገልጋዮች ስቀው አገልግሎት የሚያገኙበት ተቋም ነው።

6
ባሕር ዳር፡ የካቲት 02/2018 ዓ.ም(አሚኮ) በመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ መንግሥት ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ከእነዚህ ሥራዎች መካከል የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት አንዱ ነው።
የአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ አሥኪያጅ ተማረ አቤ ቀደም ሲል በመንግሥት ተቋማት ላይ የተንቀራፈፈ እና ተገልጋዮችን እንዲያማርር ያደረገ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንደነበር ተናግረዋል። በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመንግሥት ተቋማት እየተስተዋለ የመጣው ከእጅ መንሻ ያልተላቀቀ ብልሹ አሠራርም ፈታኝ መኾኑንም አንስተዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍ እና ለሕዝቡ የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት መሶብ የአንድ ማዕከል የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋም መቋቋሙን ነው የገለጹት።
መንግሥታዊ አገልግሎት ፈላጊዎች መሶብ የአንድ ማዕከል “አገልግሎት ተሳቀው ሳይኾን ስቀው አገልግሎት የሚያገኙበት ተቋም መኾኑንም” ገልጸዋል።
የአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሁን ላይ 10 የክልል እና አራት የፌዴራል በድምሩ 14 ተጠሪ ተቋማትን ይዞ የተደራጀ መኾኑንም አንስተዋል። አሁን ላይ ማዕከሉ ከ61 በላይ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በመለየት፣ በማደራጀት እና ዲጂታላይዝ በማድረግ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ነው የጠቀሱት።
አሁን ላይ በማዕከሉ የገቡት ተቋማት ለተገልጋዮች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ተቋማቱ መጀመሪያ ወደ ማዕከሉ ሲገቡ ይዘዋቸው ከገቡት አገልግሎቶች በተጨማሪ ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶችን ጭምር በማካተት ለተገልጋዮች ቀልጣፋ እና ተደራሽ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡
በርካታ አገልግሎት ፈላጊዎች በማዕከሉ እየተገለገሉ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ተገልጋዮችም በማዕከሉ ባገኙት አገልግሎት ደስተኛ መኾናቸውን እንደሚገልጹላቸው አንስተዋል።
በአማራ ክልል መሰብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የንግድ ባለሙያ በመኾን እየሠራች የምትገኘው ሃሲና ማሩፍ በማዕከሉ የሚሰጡ መንግሥታዊ አገልግሎቶች በቴክኖሎጅ የታገዙ በመኾናቸው የተገልጋዮችን ብቻ ሳይኾን የባለሙያዎችን ድካም የሚቀንሱ መኾኑን ነግራናለች።
ቀደም ሲል በማዕከሉ በ10 ደቂቃ ደንበኞችን የማስተናገድ አሠራር ተሻሽሎ በሁለት ደቂቃ ማስተናገድ እየተቻለ መኾኑንም ነው የገለጸችልን።
እርሷ ካለችበት ሥራ ዘርፍ አኳያ ተገልጋዮች ወደ ማዕከሉ መምጣት ሳይጠበቅባቸው የንግድ ፈቃድ ምዝገባ፣ እድሳት እና ስረዛ አገልግሎቶችን ባሉበት ቦታ ኾነው ሲስተም ላይ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ዕድል እንዳለም ጠቅሳለች።
በሲስተሙ ላይ ግን ለተገልጋዮች ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅ ነው የጠቀሰችው።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የሪፎርም ክትትል እና ድጋፍ ዳይሬክተር እንዳላማው ይታይህ የተመረጡ ተቋማት በማዕከሉ አገልግሎት እየሰጡ እንደኾነ ተናግረዋል።
ተቋማት ብቻ ሳይኾኑ የተሻለ ሙያዊ ብቃት እና ሥነ ምግባር ያላቸው ሙያተኞች ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ መደረጉንም አስታውሰዋል።
በማዕከሉ በተዘረጉ ሲስተሞች እና ቴክኖሎጂዎች ላይም ባለሙያዎች ሥራ ከመጀመራቸው በፊት እና በሥራ ላይ እያሉ ሥልጠናዎች ሲሰጣቸው መቆየቱን ጠቅሰዋል።ይህም የሚቀጥል ተግባር መኾኑን ነው ያነሱት።
አሁን ላይ ወደ ማዕከሉ ያልገቡ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ወደ ማዕከሉ ለማስገባት በጥናት የመለየት እና ተያያዥ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ነው የጠቀሱት።
ቀጣይም ብቃት እና ሥነ ምግባር ያላቸው ሙያተኞችም ተለይተው የሚገቡ ይኾናልም ብለዋል።
ተገልጋዮች ሲስተሞችን ተጠቅመው እና ባሉበት ቦታ ኾነው አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችሉ ሲስተሞችን ሚዲያዎችን ጨምሮ በተለያዩ አማራጮች የማስተዋወቅ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበ2018 በጀት ዓመት ለ1 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።