
ባሕር ዳር: የካቲት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በሰቆጣ ከተማ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ የተገነባውን ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የዳሎል ማዕከላዊ እዝ ሀገርን በጀግንነት ከማጽናት ባሻገር ዘመናዊ ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት አስገንብቶ ማስረከቡን ተናግረዋል። ሠራዊቱ ሀገርን ለማጽናት ለከፈለው መስዋዕትነት እና ለቤተ መጻሕፍቱ ግንባታ ምስጋና ይገባዋል ነው ያሉት።
ዋግ በሀገር ግንባታ ትልቅ ታሪክ ያለው መኾኑን ገልጸዋል። የዋግ ሕዝብ የጽናት ተምሳሌት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች በመቋቋም ሀገር በማጽናት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መኾኑን ተናግረዋል።
የዋግ ሕዝብ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው፣ የሀገር ዳር ድንበር የሚያስከብሩ ጀግና ወታደሮችን ያፈራ መኾኑን ተናግረዋል። የዋግ ሕዝብ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመቋቋም ሀገር እንዳሻገረ ገልጸዋል።
የዋግ ሕዝብ ሀገር በማጽናት የተጫወተውን የጀግንነት ታሪክ የሀገር ዋነኛ ጠላት የኾነውን ድህነት በመዋጋትም ታሪክ መድገም አለበት ነው ያሉት።
በጦርነት የያሳየውን ጀግንነት በደኅንነት ትግል ላይ መድገም እንዳለበት አሳስበዋል። ከችግር የመውጫ መንገድ ልማትን ማረጋገጥ እንደኾነም ተናግረዋል።
ለልማት በጽናት መታገል እንደሚገባ ተናግረዋል። ልማታቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ሉዑላዊነት አጽንተዋል፤ እኛም በጀግንነት ሀገርን እንደጠብቅን ሁሉ ድህነትንም በመታገል ሀገራችንን ማበልጸግ አለብን ነው ያሉት።
የእድገት መሠረቱ እና መግቢያ በሩ የሰው ኃይል ልማት ነው፤ የዳሎል ማዕከል ዕዝም ይሄን ለማረጋገጥ ቤተ መጻሕፍት አስረክቦናል ብለዋል። ቤተ መጻሕፍቱ የሚያስፈልጉት ግብዓቶች እንዲሟሉ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር እና የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
